የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ የህዝበ ዉሳኔ ድምፅ መስጫ ቀን ህዳር 3/2012 እንዲሆን መወሰኑን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ የህዝበ ዉሳኔ ድምፅ መስጫ ቀን ህዳር 3/2012 እንዲሆን መወሰኑን ምርጫ ቦርድ ዛሬ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣዉ መግለጫ አስታወቀ፡፡

ቦርዱ ከነሃሴ 20፤ 2011 እስከ ህዳር 10፤ 2012 ድረስ የሚቆይ የህዝበ ዉሳኔዉን የድርጊት መርሃግብር እና በጀት አዘጋጅቶ ለደቡብ ክልል ምክር ቤትና ሌሎች የሚመለከታቸዉ አካላት መላኩንም አመልክቷል፡፡

በድርጊት መርሃግብረሩ መሰረትም የባለድርሻ አካላትን ማስተባበርና የአፈፃፀም ዉይይት የማድረግ ስራ ከነሃሴ 30 ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሳምንታት የሚከናወን ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የ8460 ምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላና 1692 የምርጫ ጣቢያዎችን የማደራጀት ስራ እንዲሁም የህዝበ ዉሳኔ መመሪያዎችን የማውጣትና የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመትና የመሳሰሉት ስራዎች እንደሚከናወኑ የቦርዱ መግለጫ አዉስቷል፡፡

ቦርዱ በተጨማሪም ከመስከረም 07 ቀን 2012 አ.ም ጀምሮ የህዝበ ውሳኔውን ጸጥታና ደህንነት ጥበቃ የእቅድ ዝግጅት ለማከናወን ከፌደራል፣ ከክልል እና ከዞን የጸጥታ አካላት ጋር የጋራ እቅድ የማውጣት ውይይቶችን ያደርጋል፡፡

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የሀዋሳን ከተማ የወደፊት ሁኔታ ፤የሀብት ክፍፍል እና የሌሎች ብሄረሰብ አባላትን የመብቶች ጥበቃ አስመልክቶ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ ማእቀፎችን ማውጣት ስራ እስከ መስከረም 22 ድረስ እንዲያጠናቅቅ መታቀዱንም የቦርዱ መግለጫ ያሳያል፡፡

ቦርዱ የቴክኒክ ጉዳዮች በቀሪው ጊዜ ሲያጠናቅቅ ባለድርሻ አካላትም በተሰናዳው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በመወጣት ሕዝበ ውሳኔው በታቀደለት ጊዜ መሰረት እንዲከናወን የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አስታውቋል፡፡