የቀድሞው ማዕከላዊ እስር ቤት ለጉብኝት ክፍት ሊደረግ ነው

ጳጉሜን 5 ቀን 2011 ዓ.ም የሚከበረውን የፍትህ ቀን ምክንያት በማድረግ የቀድሞው ማዕከላዊ እስር ቤት ለጉብኝት ለህዝብ ክፍት እንደሚደረግ የበዓሉ የኮሚዩኒኬሽን፣ ሚድያና መድረክ ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዝናቡ ቱኑ ገልፀዋል፡፡

እስር ቤቱ ከዚህ ቀደም በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈጸምበት እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ ለውጡን ተከትሎ እንዲዘጋና ወደ ሙዚየምነት እንዲቀር መወሰኑ ይታወቃል፡፡

ኮሚቴው እንዳለው በማእከላዊ እስር ቤት በፖለቲካ ነክ የህግ ተጠያቂ እስረኞች ላይ የማይሽር የስነ-ልቦና ጥቃትና እስከ አካል መጉደል የሚያደርስ ቶርቸር ይፈጸምባቸው እንደነበር አስታውሶ ኢቢሲ ነው የዘገበው፡፡

በተጨማሪም በተጠርጣሪዎች ላይ የምርመራ ሂደት ሲከናወን በጨለማ ቤት ተዘግቶባቸው ከፍተኛ የሆነ በደል ይደርስባቸው አንዳንዶችም ህወታቸው ያልፍ ነበር፡፡

ከለውጡ ወዲህ እስር ቤቱ ተዘግቶ በቦታው ላይ ይፈጸም የነበረው የተጠርጣሪዎች የሰብአዊ መብት ጥሰት ቆሟል፡፡

እናም አሁን የፍትህ ቀንን ምክንያት በማድረግ ከጳጉሜን 1 እስከ 4 ቀን 2011 ዓ.ም እስርቤቱ ለጉብኝት ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ኮሚቴው አስታውቋል።