የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤታቸው አማካኝነት በምርጫ ህጉ ላይ ሳንወያይ ህጉ ጸድቋል ያሉት ተቀባይነት የለውም-ቦርዱ

የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤታቸው አማካኝነት በምርጫ ህጉ ላይ ሳንወያይ ህጉ ጸድቋል ያሉት ተቀባይነት የለውም-ቦርዱ

የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤታቸው አማካኝነት በምርጫ ህጉ ላይ ሳንወያይ ህጉ ጸድቋል ያሉት ተቀባይነት የለውም ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልል ምርጫ ቦርድ አደረጃጀትን እና የክልል የምርጫ ሃላፊዎች ምልመላ በተመለከተ እና የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ሂደትን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤታቸው አማካኝነት በምርጫ ህጉ ላይ ሳንወያይ ህጉ ጸድቋል ያሉት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን፤ ህጉ በተከታታይ ጊዜ ውይይት የተደረገበት መሆኑን በመጠቆም ነው፡፡

በመግለጫቸውም በቅርቡ የፓለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ያቀረቡበት የምርጫና የፓለቲካ ፓርቲዎች ህግ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ በሀገሪቱ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ፓርቲዎች በተገኙበት ሶስት ጊዜ አስፈላጊው ውይይት የተካሄደበት መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዋና መስሪያ ቤት ደረጃ የጀመረውን ውስጣዊ አደረጃጀት ሪፎርም በክልል ደረጃ በማስፋት በ9 ክልሎች የሚገኙት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹን እንደአዲስ እያደራጀ እንደሚገኝም በማስታወቅ፤ ቦርዱን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ 1133/2011 መሰረት የክልል የምርጫ ቦርድ ሃላፊ ለመሆን የሚፈልጉ መሰፈርቱን በማሟላት መወዳደር ሚችሉ መሆኑም ገልጿል፡፡

ቦርዱ የሲዳማ ዞን ህዝበ ውሳኔ አፈጻጸምን በማስመልከት የስራ እቅድ እና በጀት ያዘጋጀ መሆኑን ገልጸው፤ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውንም ውይይት ከነሃሴ 30/2011 አ.ም ጀምሮ በተከታታይ የሚያከናውን መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሀዋሳ ከተማን ጨምሮ የሀብት ክፍፍልን በተመለከተ የህግና አስተዳደር ጉዳዮች ከመስከረም 22 ቀን 2012 በፊት እንዲቀርብ ስምምነት መደረሱን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ለሚካሄደው ምርጫ 250 ሺህ የምርጫ አስፈፃሚዎች እንደሚመለመሉ የሚጠበቅ ሲሆን ይህንን ገለልተኛ ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ምርጫ ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ይመርጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።