የክልሉን ፖሊስ ለማዘመን እንደሚሰራ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

 የፖሊስ ኃይሉን ወቅቱን በሚመጥን መልኩ ለማደራጀት እና ለማዘመን ማቀዱን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የአማራ ክልል መንግስት ያለ ሠላም ልማት እንደማይኖር በመረዳት የክልሉን የጸጥታ ኃይል ወቅቱን በሚመጥን መልኩ ለማደራጀት ማቀዱን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ለአብመድ አስታውቀዋል፡፡

የማዘመን ሥራውም የሕዝቡ ቁጥር መጨመርን፣ የኢንዱስትሪዎች፣ የከተሞች እና የትምህርት ተቋማት መስፋፋትን፣ የሆቴሎች እንዲሁም የጎብኝዎች ቁጥር መጨመርን ጋር ታሳቢ እንደሚያደርግ ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት፡፡

በዚህም ከክልሉ አልፎ ሀገር ሊጠብቅ የሚችል የጸጥታ ኃይል በአዲስ መልክ ለመገንባት ዕቅድ መያዙን፣ ተግባራዊ ለማድረግም ጥናቱ መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

በጥናቱ መሠረትም የኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝም፣ የእሳት አደጋ እና የባሕር ኃይል ፖሊስ በመገንባት ለሀገሪቱ አዲስ አሠራር ለማሳየት ታቅዷል፡፡ የቱሪዝም ፖሊስ ጎብኝዎች ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲጎበኙ የማድረግ ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ የኢንዱስትሪ ፖሊሶች ሥራ ጀምረዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ባሉበት ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በማስፋትም ፋብሪካዎችን ከጥቃት እንዲከላከል ይሠራል፡፡ በ2012 ዓ.ም ጀምሮ ይህንን ለማድረግ እንደሚሠራም ነው ኮሚሽነር አበረ የተናገሩት፡፡

የክልሉን የጸጥታ ኃይል የደንብ ልብስ፣ የደሞዝ እና የጥቅማጥቅም ልዩነት ለማስተካከል ሲሰራ መቆየቱን የገለፁት ኮሚሽነሩ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ሥራ የሚሆነውም ይህንን ማስተካከል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ዓለማቀፍ ገጽታ ያለውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለማስቆም እየተሰራ ስለመሆኑም ኮሚሽነር አበረ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ምሁራን፣ የኃይማኖት አባቶች እና መላው የክልሉ ሕዝብ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን መቆም ህግን እንዲያስከብርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡