የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሲሰራቸው የነበሩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማጠናቀቁን አስታወቀ

የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሲሰራቸው የነበሩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ በዋናነት ከወሰን አስተዳደር፣ ራስን በራስ ከማስተዳደርና ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ላይ በጥናት ላይ የተመሰረቱ የውሳኔ ምክረ ሀሳቦችን ለማቅረብ ታስቦ የተቋቋመ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

እስካሁንም በቅድመ ዝግጅት ስራው የአደረጃጀት፣ የግብዓት፣ የሰው ሀይል የሟሟላት፣ የአባላት ስነ-ምግባርና ስትራቴጂክ እቅድ የማዘጋጀት ስራዎች መስራቱን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ጣሰው ገብሬ እና ምክትል ኮሚሽነሩ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በስትራቴጂክ እቅዱ የማንነትና የወሰን አስተዳደር፣ ራስን የማስተዳደርና የተቋማት ግንባታ መሰረት ያደረጉ ዋና ዋና ጉዳዮች ተካተውበታል ተብሏል፡፡

በ2012 በጀት ዓመትም በማንነትና በወሰን አስተዳደር እንዲሁም ራስን በማስተዳደር ችግሮች አሉባቸው ተብሎ በተለዩ ቦታዎች ላይ ንኡሳን ኮሚቴዎችን በማቋቋም የሚሰራ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

ኮሚሽኑ በእነዚህም ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተለይ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡