አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሩሲያው አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ተወያዩ

የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርገይ ላቭሮቭ ጋር ሞስኮ በሚገኘው የሩሲያ ፌደሬሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በሁለቱ ሀገራት ሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ እና ሩሲያ 121 ዓመታት ያስቆጠረ እና ከአድዋ ድል ማግስት በተጀመረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሠረቱ የተጣለ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን፤ ሩሲያ በጠላት ወረራ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጎን ከተሠለፉ ወዳጆች አንዷ መሆኗን አስታውቀዋል።

በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መስክም ታዋቂው ባለቅኔ አሌክሳንደር ፑሽኪን ትውልደ ኢትዮጵያዊ እና ሩሲያዊ መሆኑ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሩሲያ ነጻ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ መደረጉ ሌላው የግንኙነቱ ጠንካራነት መገለጫዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህንን በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ ወዳጅነት በቴክኖሎጂ፣ በአቪየሽን ኢንዱስትሪ እና በባህል መስኮች ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሁለቱ አገሮች በመጪው ጥቅምት ወር በሚያካሄዱት የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ ገዱ ገልጸዋል።
አቶ ገዱ የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተፈጠረው ምቹ ንግድና ኢንቨስትመንት ሁኔታ እንዲሳተፉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ሩሲያ በኢትዮጵያ የምታደርገው እንቅስቃሴ ወደ አፍሪካ ገበያ ለመግባት መንደርደሪያና ኢትዮጵያም የአፍሪካ ደጃፍ መሆኗን በመጥቀስ፤ ሩሲያ በዕድሉ ልትጠቀም እንደሚገባ አቶ ገዱ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት ለማምጣትና የኢኮኖሚ ትስስር የሚጎለብትበትን አማራጮች የማጠናከር ሥራ እየሠራች መሆኑን፤ በቅርቡም በሱዳን የተጫወተችው ዲፕሎማሲያዊ ሚና ለዚሁ ማረጋገጫና ዓይነተኛ ማሣያ መሆኑን ሚኒስትር አቶ ገዱ ገልጸዋል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ታሪካዊ ግንኙነት እንደሚያደንቁ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሩሲያ ቁልፍ አጋር ሀገር እንደሆነች በመግለጽ፤ በሁለቱ ሀገሮች መካከል በየጊዜው የሚደረጉ የሁለትዮሽ ውይይቶች ትብብሩን ወደ ላቀ ከፍታ እንደሚወስደው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በባለ ብዙ ወገን ግንኙነት መስክ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምታራምደው ኃላፊነት የተሞላው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንደሚያደንቁና ከሩሲያ ጋርም በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ በጋራ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን ሰርጌ ላቭሮቭ ገልጸዋል።

የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በሽያጭ መስክ ብቻ ሳይሆን በተሽከርካሪ መገጣጠሚያ መስክ ያላቸውን ሠፊ ልምድ ይዘው መግባት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

የሩሲያ ሳይንስ አካዳሚ ከኢትዮጵያ ጋር በባዮሎጂ መስክ የሚያደርጉትን ትብብር ለማጠናከር ያላቸውን ፍላጎት አስታውቀዋል።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አኳያም በሩሲያ የዲፕሎማቲክ አካዳሚ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች የሚሠለጥኑበትን ሆኔታ እንደሚያመቻቹ አስታውቀዋል።

በውይይቱ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሣ በቀጣይ በሁለቱ ሀገራት መካከል በመከላከያ መስክ ትብብሮች ለማድረግ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለይ በማዕድን ፍለጋና ልማት ለሁለቱም ሃገራት የጋራ ጥቅም መሥራት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትኩረት እንዲሠጥባቸው ለቀረቡት የትብብር መስኮች የቅርብ ክትትል በማድረግ ለውጤታማ ትብብር እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

(ምንጭ ፦ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር)