2011 ዓ.ም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ከማጠናከር ጀምሮ የተለያዩ ክስተቶች ተመዝግበውበታል ሲሉ ዶ/ር ደብረጽዮን ገለጹ

በተጠናቀቀው 2011 ዓ.ም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከርን ጨምሮ የተለያዩ ክስተቶች የተስተናገዱበት ነበረ ሲሉ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ የአዲስ አመት መልካም ምኞታቸውን ባስተላለፉበት ወቅት እንዳትስታወቁት፤ በተጠናቀቀው አመት በሀገሪቱ በርካታ በጎና በጎ ያልሆኑ ክስተቶች ተስተናግደዋል።

ለሀያ አመታት ተራርቀው በነበሩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች መካከል ታሪካዊ ምእራፍ የተሰራበት አመት ሆኖ መጠናቀቁንም ዶክተር ደብረጽዮን ተናግረዋል።

በሁለቱም ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ጥላቻ መወገድ የተጀመረበትና አንዱ ሌላኛውን እንደሚያስፈልገው እምነት የጣሉበት አመት እንደነበር ገልጸዋል።

ከድንበር አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ችግሮች በዘላቂነት ተፈትተው የሁለቱ ሃገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ መንግስት ፍላጎት መሆኑንም አመልክተዋል።

“ክልሉ በጥናት ላይ የተመሰረተ አዲስ የቀበሌ ቋሚ አስተዳደሮች የተመደቡበት አመት በመሆኑ ህብረተሰቡ ለበርካታ አመታት ያነሳው የነበረ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል ጅምር ስራዎች የተከናወኑበት ነው” ብለዋል።

የወረዳ አስተዳደሮችም ያላቸውን ሃብት መሰረት ያደረገ አዲስ የወረዳ አወቃቀር ጥናት ተጠናቅቆ ወደ ህዝብ ውይይት መቅረቡንም ተናግረዋል።

ይህም በህዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ጥናትን መሰረት ያደረገ መልስ ከመስጠት ባለፈ ለልማት የሚያግዝ የሰው ሀይል አመዳደብ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።

የተጠናቀቀው ዓመት በራያ ዐዘቦና ራያ አላማጣ ወረዳዎች ለአስር አመታት የህዝብ ጥያቄ የነበሩ ከ100 በላይ ጥልቅ የውሀ ጉድጓዶች ወደ ልማት ለማስገባት ጥረት የተጀመረበት እንደነበረም አስታውሰዋል።

ዓመቱ ከመንገድ ርቀው የነበሩ 149 ቀበሌ ገበሬ ማህበራት ወደ መንገድ ለማስገባት ህዝብና መንግስት በጋራ የተረባረቡበት መሆኑንም ጠቅሰው እየተንከባለሉ የመጡ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ጥረት መጀመሩንም ተናግረዋል።

በአንጻሩ የተለያዩ ሀይሎች ክልሉን አደጋ ውስጥ ለመክተት በርካታ እንቅስቃሴዎች ያደረጉበት ዓመት እንደነበረ ያመለከቱት ዶክተር ደብረጽዮን አዲሱ አመት የሰላምና የብልጽግና አመት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

መጪው አመት በርካታ ውዝፍ ስራዎች የሚጠናቀቁበት ከመሆኑም ባለፈ እንደ ሀገር አንድነትን ጠብቆ ለማቆየት ወሳኝ ስራ የሚከናወንበት መሆኑንም ጠቁመው ምርጫ 2012 ዓ.ም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚጠይቅም አመልክተዋል። (ምንጭ፡-ኢዜአ)