የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የደቡብ ሱዳን አቻቸውን አነጋገሩ

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የደቡብ ሱዳን አቻቸው አዉት ዴንግ አኩዊልን ትናንት ማምሻውን ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸው በደቡብ ሱዳን ጁባ በቅርቡ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና በዶክተር ሪክ ማቻር መካከል ውይይት መካሄዱ ለደቡብ ሱዳን ብሎም ለአካባቢው ሠላም ያለው ፋይዳ እጅግ የላቀ መሆኑን አቶ ገዱ ገልጸዋል።

የሁለቱ መሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝቶ መወያየትም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በተቀናቃኝ ወገኖች የተቀመጠውን የሰላም ፍኖተ ካርታ ለመተግበር ወሣኝ ምዕራፍ መሆኑንመም ነው የተናገሩት።

የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አዉት ዴንግ አኩዊል በበኩላቸው በደቡብ ሱዳን እየታየ ያለው ፈጣን የፖለቲካ ለውጥ በአፍሪካ ቀንድ እየነፈሰ ካለው የተስፋና የሰላም አየር ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን አንስተው፥ በለውጡ የደቡብ ሱዳን ህዝብ እጅግ ደስተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

የሁለቱ መሪዎች ውይይትም በደቡብ ሱዳን የደህንነትና የፖለቲካ ሁኔታዎች ዙሪያ ለመመካከር መልካም አጋጣሚን መፍጠሩን ነው ያመለከቱት።

ለቀጣዩ ሂደትም ጎረቤት ሃገሮችና ኢጋድ የድጋፍ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።