በባሕር ዳር ከተማ በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ሥር ዋለ

የአማራ ክልል አድማ ብተና 2ኛ ሻለቃ 1ኛ ሻምበል ምክትል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ታለማ ዳኛ ለአብመድ እንደተናሩት፤ በ20 ጆንያዎች የተቋጠረ 497 ሽጉጥ እና ወደ 46 ሺህ የሚገመት ጥይት በባሕር ዳር ከተማ በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡

ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነትና ከኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሠረት ከነዳጅ ጋር ተቀላቅሎ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ በገባ የነዳጅ ማመላለሻ ቦቴ ውስጥ ሲጓጓዝ ነው ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያው በቁጥጥር ስር የዋለው፡፡

ከትናንት ምሽት ጀምሮ በተደረገ ክትትል ነው ባሕር ዳር ከተማ ጣና ክፍለ ከተማ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያው በቁጥጥር ስር የዋለው፡፡

አሽከርካሪው ለማምለጥ ሙከራ አድርጎ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ያስታወቁት ምክትል ኢንስፔክተር ታለማ ነዳጁ ከባሕር ዳር አልፎ የሚሄድ እንደነበርና ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያውን ከቦቴው ለማውጣት የሚያገለግል ብረት ከተሽከርካሪው መገኘቱን አመልክተዋል፡፡