14ኛው የብሄረሰቦች ቀን አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በድምቀት ይከበራል ተባለ

14ኛውን የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ለውጡን ተከትሎ ያጋጠሙ ሃገራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ በሚያስችል መልኩ ለማክበር ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑ ተገለፀ።

በዓሉ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በድምቀት ይከበራል ያለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቅድመ ዝግጀቱን በማስመልከት ከ9ኙ ክልልና ከ2ቱ ከተማ መስተዳድር ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች እና የፌዴራል ተቋማት ተወካዮች ጋር በመምከር ላይ ነው።

በዓሉ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ እንደሚገኝ ያስታወቁት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ዘንድሮም ለ14ኛ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት በአዲስ አበባ እንደሚከበር መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

ህገ መንግሥቱ በፀደቀ በ25ኛ ዓመት የሚከበር መሆኑ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል ያሉት ወ/ሮ ኬሪያ የብሄር ጥላቻንና መካረርን በማስቀረት ህገ መንግሥቱን ባከበረ መልኩ እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል።

አፈ ጉባዔዋ አያይዘውም በአመለካከት ልዩነቶች ሳቢያ በሚፈጠሩ ችግሮች ህዝብ ሰለባ እየሆነ ነው ያሉ ሲሆን በዓሉ ይህንንና መሰል ችግሮችን ለማስቀረት በሚያስችል መልኩ እንደሚከበር ነው ያስታወቁት።