ጠ/ሚ ዐቢይ ከሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይቱ ወቅት የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ስለጉብኝታቸው አመስግነው፣ ዋና ዋና የልማት ጥያቄዎች አንስተዋል:: ለሥራ ፈጠራ በመሰረተ ልማት፣ በጤናና በአግሮፕሮሰሲንግ ኢንቨስትመንት ዙሪያ ጥያቄዎችን የነሱት ነዋሪዎቹ፣ የሀድያ ህዝቦችን የቆየ ልምድ በማጠናከር ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እንደሚቀጥሉ አንስተዋል::

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅሬታዎች በሚዛናዊና የጋራ እሴትና መርሆችን በማያጠፋ መልኩ መቅረብ አለባቸው ብለዋል:: የሆሳዕና ነዋሪዎች እውቀትና በክልሉ በአንድነት ለመቆየት ያነሱትን ሀሳብ አድንቀዋል:: በተጨማሪም በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የሆሳዕና ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ነዋይ በማሰባሰብ በአካባቢው ልማት ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ሲመልሱም የጉብኝቱ አካል ለሆኑት ለጤናና ለግብርና ሚንስትሮችና ለመንገዶች ባለስልጣን ኃላፊዎች ጥናት እንዲያካሂዱና ለየዘርፎቹ ቁልፍ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ አቅጣጫ አስቀምጠዋል ሲል የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።