ሚኒስቴሩ ግጭቶችን አስቀድሞ ለመለየት እና መቆጣጠር የሚያስችል ስርዓት ይፋ አደረገ

የሰላም ሚኒስቴር ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ያዘጋጀውን ብሔራዊ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የዘረጋውን ስርዓት በዛሬው ዕለት ይፋ አደረገ።

ይህ ስርዓት በአጭር የፅሑፍ ምልዕክትና መልእክትና በኢንተርኔት ዳታ ስስተም የሚሰራ ሲሆን መረጃዎችን በመለዋወጥ እና በማጣራት ግጭት በሚኖርባቸው አካባቢዎች አስቀድሞ ለማስቀረት የሚያስችል ነው ተብሏል።

ግጭቶቹ ቢፈጠሩ እንኳን በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች በመጠቀም አፋጣኝ የሆነ ምላሽ መስጠት ያስችላልም ነው የተባለው።

ለዚህ የስርዓት ዝርጋታ አለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፣ በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቶችን ከማስቀረት እና ህይወትን ከማዳን አንፃር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡

ስርዓቱ በጋምቤላ ክልል፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔርሰቦችና ህዝቦች ክልል እና በኦሮሚያ ክልል የሚተገበር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በቀጣይ የስርዓቱ ውጤታማነት ታይቶ በሌሎች ክልሎችም ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

ስርዓቱ ከቀበሌዎችና ወረዳዎች ጀምሮ እስከ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያለውን ተዋረድ በመጠቀም ግጭቶችን ከምንጩ ለማስቀረት ይሰራል ተብሏል።

በቀጣይ ለስርዓቱ ተግባራዊነት ነፃ የስልክ መስመሮችና አጭር የፅሑፍ መልዕክት መላኪያ መስመሮች ይፋ ይደረጋልም ነው የተባለው፡፡

ይህ የማስጀመሪያ ስርዓት ይፋ የተደረገው የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ አለማየሁ እጅጉ፣ የዩ ኤስ ኤድ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት በተገኙበት ነው።