አዴፓ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን በመፍጠር የክልሉን ህዝብ ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሰራ አስታወቀ

በአዲሱ ዓመት በመላ አመራሩና አባላቱ ዘንድ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በመፍጠር የአማራ ክልልን ህዝብ የዘመናት መሰረታዊና መዋቅራዊ ጥያቄዎች ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/አዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የአማራ ክልል የ2012 የድርጅትና የመንግስት የልማት እቅድ የንቅናቄ መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

የጽህፈት ቤቱ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ተተካ በቀለ እንዳስታወቁት በዚህ ዓመት በመላ አመራሩ፣ አባላቱና በህዝቡ ዘንድ አዲስ የትግልና የስራ መንፈስ ለመፍጠር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተፈጠሩ የመልካም አስተዳደርና የአገልጋይነት መንፈስ መጓደልና የህዝቡን ተጠቀሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን በተሟላ መንግድ አለመከናወን ህዝቡን ወደ ቅሬታ እንዲገባ አድርጎት ቆይቷል።

በዚህ የተነሳም በየወቅቱ በሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችና የፀጥታ ችግሮች አመራሩ እሳት የማጥፋት ስራ ላይ ተጠምዶ ዘላቂ የልማት ስራዎች እንዲጓተቱ ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል።

“የችግሮችን መንስኤ በጥልቀት በመገምገም በስትራቴጂ እንዲፈቱ ለማድረግ የአስተሳሰብ ፣ የአመለካከትና የተግባር አንድነት በመፍጠር በዘላቂነት እንዲፈቱ አዴፓ ጠንካራ የመሪነት ሚናውን በላቀ ደረጃ ለመወጣት ተዘጋጅቷል” ብለዋል።

“በመሆኑም በህዝብ ዘንድ በተደጋጋሚ የሚነሱ የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሃዊ ተጠቃሚነትና መሰል ጥያቄዎች የአመራሩን ብስለትና ቁመና በማዳበር በሂደት እንዲመለሱ ይደረጋል”ብለዋል።

“ህዝብን ማገልገልና ሀገርን በመለወጥ ጎዳና መምራት የአመራሩ ቁልፍ ሚና ነው” ያሉት ኃላፊው ይህን በመረዳትም አመራሩ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ መሰረት የሚጣልበት ዓመት እንደሆነም አብራርተዋል።

“አዴፓ እንደ ድርጅት ውስጣዊ አንድነቱን በማጠንከር ልማትና ሰላም ፈላጊውን ህዝብ አደራጀቶ በመምራት ክልሉ የእድገት ማማ ላይ እንዲወጣ የሚያግዙ ተጨባጭ ተግባራት ይከናወናሉ” ብለዋል።

የህዝቡ ዘላቂ ፍላጎትና ጥቅም እንዲከበርም አዴፓ ከሚያደርገው ጠንክራ ትግል ጎን ለጎን ባለሃብቱና ምሁራን ህዝባቸውን ለማገልገል እያሳዩት ያለው ቁርጠኛነት በመደጋገፍ ላይ ተመስርቶ ወደ ላቀ ውጤት እንዲመዘገብ ይደረጋል ብለዋል።

ስቪል ሰርቫንቱም ህዝቡን የሚያማርሩ የአገልግሎት መጓደልን ችግሮችን በመፍታት ምስጉንና ደረጃውን የጠበቀ ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ለለውጡ ዋና አጋዥ እንዲሆንም ተለይቶ ይሰራል ብለዋል።

በዚህ ዓመት የሚከናወነውን ሃገራዊ ምርጫ ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ ስራዎችን በስኬታማነት ለማከናወንም አመራሩን የማደራጀት ስራ መጀመሩንም አስታውቀዋል።

አሁን በከፌዴራል እስከ ወረዳ ባለው አመራር የተጀመረው የፖለቲካ ፣ የድርጅትና የመንግስት አቅድ ትውውቅም በቀጣይ እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር ውይይት በማድረግ ጠንካራ አንድነትን ለመፍጠር የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል።

የእቅድ ትውውቁ ትናንት በቡድን ተከፋፍሎ ሲካሄድ የዋለ ሲሆን በዛሬው እለት ደግሞ በሃይል መድረክ በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እየተደረገ ይገኛል። (ምንጭ፡-ኢዜአ)