ኔቶ የአፍሪካ ቀንድ ሰላምን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንደሚሰራ አስታወቀ

የኢፌዲሪ ሰላም ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዲኤታ ወ/ሮ አልማዝ መኮንን የሰሜን አትላንቲክ የቃል ኪዳን ሀገሮች ድርጅት (ኔቶ) ንዑስ-ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑትን ሚሮ ኮቫችን እና ከልዩ ልዩ ሀገራት የተውጣጡ የድርጅቱን የፓርላማ አባላት በሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
በውይይታቸውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሀገሪቱን ሰላም ከማስጠበቅ አፃር በርካታ ስራዎች እየተሰራ እንደሆነ እና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጋር ሰላማዊ የሆነ ግንኙነትን በዘላቂነት ይዛ ለመጓዝ እንድትችል በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ እንዳሉ አስረድተዋል፡፡
ሊቀመንበሩ ሚሮ ኮቫች በበኩላቸው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሀገሪቱን ሰላም ከማስጠበቅ አንፃር እየተሰራ ያለውን ስራ አድንቀው በቀጣናው ሰላምን ለማስፈን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎቱ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ  መንግሥት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን እንዲኖርና ዜጎች ዋስትናቸው የተጠበቀ እንዲሆን ልዩ ልዩ ሥራዎችን እያከናወነ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራትም እንዲሁ ይህንን ለመተግበር መትጋቱ ለሉላዊ ሰላም የሚያበረክተው አስተዋጾ የላቀ መሆኑን የልዑካን ቡድኑ አስምሮበታል፡፡
ሁለቱ ተቋማት ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ሰላም በዘላቂነት ለማስፈን የሚያስችሉ የትብብር አቅጣጫዎች ላይ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማህበራዊ መገናኛ ገፅ ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል፡፡