በሲዳማ የህዝብ ውሳኔ ጥቅም ላይ በሚውሉ ምልክቶች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ነው

የሲዳማ ዞን ክልል ሆኖ ለመደራጀት በሚካሄደው የህዝብ ውሳኔ ጥቅም ላይ በሚውሉ ምልክቶች ውይይት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

በምልክቶቹ የመጀመሪያው ረቂቅ ላይ ለመወሰን የደቡብ ክልል ምክር ቤት ውይይት እየተደረገ መሆኑን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኮምዩኒኬሽንስ አማካሪ ወ/ት ሶሊያና ሽመልስ ተናግረዋል፡፡

በህዝበ ውሳኔው የሚቀርቡ ምልክቶቹ ምን አይነት ይሁኑ በሚለው እና ምልክቶቹ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ገለልተኛ፣ የማህበረሰቡን ምስል የሚያሳዩ እንዲሁም ጥያቄዎቹ ግልጽ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡

በውይይቱ ላይ ስምምነት የተደረሰባቸው ምልክቶች ለህዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ተጠቁሟል፡፡

የህዝበ ውሳኔው አፈጻጸሞች በክልሉ ጥያቄ ለተወሰኑ ቀናቶች ከተራዘሙት ውጪ አብዛኞቹ በተያዘላቸው መርሀ ግብር እየተከናወኑ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

የህግ አስፈጻሚ እና የጸጥታ አካላት እንዲሁም የቦርዱ የስራ አመራር አባላት የህዝበ ውሳኔውን አፈጻጸም ሰላማዊነት ለማረጋገጥ ውይይት ማካሄዳቸው ታውቋል፡፡

የድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ፣ እንዲሁም የድምፅ መስጫ እና ድህረ ምርጫ ሂደቱን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የህግ አስፈጻሚ አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግ ቦርዱ ለተሳታፊዎቹ ማስገንዘቡ ተገልጿል፡፡

ለህዝበ ውሳኔ ምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና በአዲስ አበባ ከተማ ከመስከረም 24 እስከ 30 ከተሰጠ በኋላ እንደሚሰማሩም የኢቢሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡

በቀጣይ የሚካሄዱ ተግባራትም በመርሃ ግብሩ መሰረት ለማከናወን ዝግጅቶች እየተካሄዱ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ህዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ህዝበ ውሳኔ አማራጭ ሃሳቦችና የሚወከሉበት ምልክቶችን ይፋ አድርጓል

በዚህም መሰረት “ሲዳማ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ እንዲቆይ እፈልጋለሁ” ለሚለው አማራጭ የጎጆ ቤት ምልክት፣  “ሲዳማ ራሱን ችሎ በክልልነት እንዲደራጅ እፈልጋለሁ” ለሚለው አማራጭ የሻፌታ ምልክት ሆኖ ለህዝበ ውሳኔው ድምጽ መስጫነት እንዲያገለግል ተወስኗል ።