የብሄር ብሄረሰቦች ቀን አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እንዲከበር ዝግጅት እየተደረገ ነው- የፌዴሬሽን ምክር ቤት

የዘንድሮው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል አከባበር ኢትዮጵያዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እንዲሆን የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።

ለ14ኛ ጊዜ የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰብ በዓል የዝግጅት አስመልክቶ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤና የበዓሉ አዘጋጅ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሬያ ኢብራሂም እንደተናገሩት ላለፉት 13 ዓመታት የተከበረው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ጠንካራም ደካማም ጎኖች ነበሩት።

በምክር ቤቱ ዕውቅና የተሰጣቸው 76 ብሔሮችና ብሔረሰቦች ማንነታቸውን፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ማስተዋወቅ የቻሉበት አጋጣሚ በጥሩ ጎኑ ይጠቀሳል።

ኢትዮጵያ ሲባል የተለያዩ ማንነቶች፣ ባህልና እሴቶች ውህድ መሆኗን በአደባባይ ማሳየት የተቻለበት ጥሩ አጋጣሚም ነበር ብለዋል።

በዓሉን ተሰባስቦ የተለያዩ ማንነቶች፣ ባህልና እሴቶችን ከማስተዋወቅ ባለፈ፤ ልዩነቶቻችን ለአንድነታችን ውበት ሆነው እንዲጎሉ በማድረግ ላይ ግን ክፍተት ነበር ብለዋል ወይዘሮ ኬሪያ።

የዘንድሮው በዓል አከባበር ግን ባለፉት ጊዜያት የነበሩትን ክፍተቶች በመሙላት ጠንካራ ጎኑን በማስቀጠል የሚከወን መሆኑን ገልጸዋል።

አከባበሩ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እንዲሆን የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑንም አፈጉባዔዋ ተናግረዋል። (ምንጭ፡-ኢዜአ)