የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት ተስማሙ

የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከ5 ወራት በላይ ከተደራደሩ በኋላ አብረው በጋራ ለመስራት ተፈራርመዋል፡፡

እነዚህ ፓርቲዎች በህዝብ ጉዳይ ላይ በከፍተኛ ትብብር አብረው ለመስራት ነው ከስምምነት የደረሱት፡፡

ፓርቲዎቹ በጋራ ባወጡት የአቋም መግለጫ፣ መጪው ምርጫ ፍትሓዊና ነፃ እንዲሆን ለማድረግ አብረን እንሰራን፣ ከ150 ዓመታት በኋላ የሚከበረው የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ትግል ውጤት በመሆኑ ህዝባችን በዓሉን በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት እንዲያከብር እንመኛለን ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ODP) ሊቀመንበር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በስምምነቱ ወቅት "ኦሮሞ በጋራ ተሰባስቦ በሀሳብ መሸናነፍ፣ እርስ በርስ መመካከርና መስማማት አዲስ አይደለም፣ ባህላችን ነው፣ መወያየት፣ እርስ በርስ መማማር በጣም ወሳኝ ነው" ብለዋል፡፡

መጪው ምርጫ ነፃና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን እንሰራለን፣ ይህ ስምምነታችን ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ተሻግሮ ከሌሎች ጋር በእኩልነትና በነፃነት አብረን መኖር የምንችልበት ሁኔታ ላይ ማተኮር አለብን ብለዋል ዶ/ር ዐቢይ፡፡

በስምምነቱ ላይ የODP ም/ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦሮሚያ ክልል ም/ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ ብ/ጄኔራል ከማል ገልቹ፣ አቶ ሌንጮ ለታና የሌሎች የኦሮሞ ፓርቲ አመራሮች መገኘታቸውን ከOBN ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡