የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው

የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ጥቅምት ወር ላይ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ እንደሆነ ተገለፀ፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በአፍሪካ በሚያደርጉት ጉብኝት ከአዲስ አበባ ባሻገር የደቡብ ሱዳንን ጁባ ከተማ እንደሚጎበኙ ተነግሯል፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በጥቅምት 12 እና 13 በአዲስ አበባ በሚያደርገው ቆይታውም ከአፍሪካ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት እና ከአጋር አካላት ጋር ዓመታዊ ምክክር እንደሚያደርግ ተመልክቷል፡፡

በማግስቱም ምክር ቤቱ በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ኬሊ ክራፍት ጋር በመሆን በጁባ ጉብኝት እንደሚያደርግ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

በዚህም በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ በተቀመጡ የውይይት አጀንዳዎች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ነው የተነገረው፡፡

ምክር ቤቱ አፍሪካ የሚያደርገውን ጉብኝት ካጠናቀቀ በኋላም በኒውዮርክ በሚያደርገው ስብሰባ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም በኮሶቮ ጉዳይ ላይ ውይይት እንደሚያደርግ ተጠቁሟል፡፡ (ምንጭ፡-ሽንዋ)