የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ ተቀየረ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ለበርካታ ጊዜ ሲጠቀምበት የነበረውን የደንብ ልብስ በአዲስ ዘመናዊ የደንብ ልብስ ተቀይሯል፡፡

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ አዲሱን የአዲስ አበባ የፖሊስ አባላት የደንብ ልብስ መርቀዋል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የከተማዋን ሰላም እና ደህንነት ለመጠበቅ ጠንካራ ስራ እየሰራ ያለውን የአዲስ አበባ ፖሊስ የማዘመን ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዘላቂነትም የከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባን የሚመጥን ዘመናዊ እና የተደራጀ የፖሊስ ሰራዊት ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ምክትል ከንቲባ ተናግረዋል፡፡

የተመረቀው የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ የኮሚሽኑ አርማ ያለበት ሲሆን በሂደት ለሁሉም አባላት እንደሚሰራጭ ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡