ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ልዩ መልእክተኛን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራምፓሳ ልዩ መልእክተኛ የሆኑትን ጄፍ ራዴብ እና ዶ/ር ኩሁሉ ባታን ጠዋት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ::

ልዩ መልእክተኞቹ የፕሬዝዳንት ሲሪል ራምፖሳን የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት ያነሳውን መልእክት ሲያስተላልፉ ግንኙነቱን ወደ ስትራቴጃዊ ደረጃ ከፍ ለማድረግም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በደቡብ አፍሪካ ኦፊሴላዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል::

በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እና ዝርፊያ በበቂ ለመከላከል መንግሥታቸው እየሰራ መሆኑን የገለፁት መልእክተኞቹ እዛ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እየተጫወቱት ያለውን በጎ ሚናም አድንቀዋል::

በተጨማሪም መልእክተኞቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እስረኞችን በመፍታትና ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ላሳዩት የአመራር ብቃት ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት ማሳያዎች ጠቅሰዋል:: ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ የኢኮኖሚ እድገትና ዴሞክራሲ እድገት ማሳያ መሆኗንም አድንቀዋል::

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ አትዮጵያውያን በሚኖሩበትም ሆነ በሀገራቸው ኢትዮጵያ እየተጫወቱ ያለውን ሚና በማንሳትም የደቡብ አፍሪካ መንግስት ይህንኑ ትጋታቸውን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል:: (ምንጭ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት)