​​​​​​​ከ2 ሺህ በላይ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በነዳጅ ማመላለሻ ቦቴ ተጭኖ የነበረ ከ2 ሺህ 200 በላይ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች እና አሽከርካሪው ጎንደር ከተማ ላይ ትላንት ማምሻውን በቁጥጥር ስር ውለዋል።

አሽከርካሪው የጦር መሳሪያዎቹን በመጫን መነሻውን ከሱዳን አድርጎ ወደ ጎንደር ሲገባ እንደተያዘ ከስፍራው የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በተደረገ ቆጠራ 2 ሺህ 221 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ፣ 34 ባለ ሁለት እግር ታጣፊ ክላሸንኮቭ፣ አንድ ባለ አንድ እግር ታጣፊ ክላሸንኮቭ፣ 35 ባለሰደፍ ክላሸንኮቭ እና አንድ ጄ ኤም-3 እንደተያዘ ታውቋል።

የጦር መሳሪያዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ሰራተኞች እና በአማራ ክልል የሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ በጥምረት እንደሆነ ተገልጿል።

ህብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ፣ ለፀጥታ አስጊ እና አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከትም ለፀጥታ ኃይሉ እንዲያሳውቅ የክልሉ የሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ጥሪ አቅርቧል። (መንጭ፡-አብመድ)