የምክር ቤቶቹ የጋራ ስብሰባ በይፋ ተከፈተ

የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን በይፋ ተከፍቷል። 

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ንግግር ያቀረቡ ሲሆን፣ 2012 ዓ.ም የለውጡን ጉዞ የተሻለ መሠረት የምናስይዝበት ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አነሳሽነት በመተግበር ላይ የሚገኘውን የመደመርን እሳቤ መሠረት አድርጎ እንደሚጓዝና በሦስት ዋነኛ ሀገራዊ ዓላማዎች ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሀገሪቱ የነበሩ መልካም የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድሎችን ጠብቆ ማስፋት፣ ባለፉት ዘመናት የተሠሩ ስህተቶችን ማረምና የመጭውን ትውልድ ፍላጎትና ጥቅም ማሳካት ናቸው ብለዋል ፕሬዝዳንቷ፡፡

ያለፈው ዓመት በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙና ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ እንዲተገበር ጥረት የተደረገበት ወቅት እንደነበርም አንስተዋል፡፡

በፖለቲካ፣ በዴሞክራሲ፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ፣ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ በፍትሕ ሥርዓት እና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የነበረብንን ሀገራዊ ጉድለት ማስተካከል የተጀመረበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ይሁንና ጉድለቱን በተሟላ ያቃናንበት ደረጃ ላይ ገና አልደረስንም ያሉት ፕሬዝዳንቷ፣ አንዳንዶቹም በባሕሪያቸው መዋቅራዊ በመሆናቸው ከአንድ ዓመት አለፍ የሚል ምክንያታዊ ጊዜን የሚጠይቁም ናቸው ብለዋል፡፡

የደኅንነትና የጸጥታ ተቋማትን እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊትን የሕጋዊ ማዕቀፎችና አቅሞችን በማዳበርና በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግ በሀገሪቱ ያለውን አንጻራዊ ሠላም ወደ አስተማማኝ ሠላም ለማሳደግ በትኩረት ይሠራል ሲሉ ተናገረዋል፡፡  

በቀጣይ ሀገሪቱ የምታስተናግዳቸውን ሀገራዊ ምርጫ እና ሌሎች ክስተቶች ሠላማዊ በሆነ መልኩ ለመፈጸም የሚያስችል አቅም ይፈጠራልም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት የተሰደዱትን ማስተናገዷን የቀጠለችውን ያህል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ተፈናቃይ የሆኑበትን አሳዛኝ የታሪክ ገጽ አልፈናል ያሉት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ባለፈው አንድ ዓመት በጋራ ባደረጉት ርብርብ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የነበረው የውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ከመቶ ሺ የማይዘል እንደሆነ ገልጸዋል።

“ያለፍንባቸው የታሪክ ምዕራፎቻችን መልካም ጸጋዎች እንዳሉት ሁሉ በርካታ ስህተቶችም እንዳሉት የጠቆሙት ፕሬዝዳንቷ፣ እኩልነትን፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብትን፣ አካታችነትን፣ የሰብአዊ መብት አያያዝን፣ የፍትሕ ሥርዓት መዛነፍን በተመለከተ የተፈጸሙ ስህተቶች እንዳሉ ተናግረዋል።

“በቅርቡ ታሪካችን እንኳን ልዩነቶቻችን ላይ የሠራነውን ያህል አንድነታችን ላይ አልሠራንም፣ የኢኮኖሚ እድገቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በሚገባው ልክ አላረጋገጠንም፣ በሰብአዊ መብት አያያዛችንና በፖለቲካዊ መብቶቻችን ላይ ሰፊ ጉድለቶች ተመዝግበዋል። እነዚህ የተወዘፉ ዕዳዎቻችን ናቸው። ውዝፍ ስህተቶቻችንን ያለ ምሕረት ማረም ይኖርብናል” ሲሉም አንስተዋል፡፡