ምርጫን ፍትሃዊና ተዓማኒ ማድረግ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ጉዞ የማቃናት ሚናው ከፍተኛ ነው-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

በተያዘው ዓመት ሊካሄድ በታቀደው ሀገራዊ ምርጫ ዙሪያ ያተኮረ አለምአቀፍ ምክክር እየተካሄደ ነው፡፡

ኮንፈረንሱ ቀጣዩ ምርጫን እንዴት ነጻ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ ማድረግ ይቻላል፣ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አባል ማሻሻያና የምርጫ ዝግጅት እና በሌሎችም ነጥቦች ላይ በመምከር ላይ ይገኛል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ምርጫን ፍትሃዊ እና ተዓማኒ ማድረግ ሀገሪቱ የጀመረችውን ለውጥ ለማሳካትና ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ጉዞ የማቃናት ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል ፡፡

እስከ ነገ በሚቆየው በዚህ መድረክ በአዲሱ የምርጫ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ የመንግሥት ግዴታና የፖለቲካ ፖርቲዎች መብት የሚሉ ጭብጦችን ጨምሮ በመጭው ምርጫ ወቅት ሠላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ መወሰድ ያለባቸዉ ሁኔታዎች ላይ ምክክር ይደረጋል፡፡

በዚህ የምክክር መድረክ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የብዙሃን መገናኛ ተቋማትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች አካላት እየተሳተፉ ይገኛል፡፡