ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ያቀረበችው የመነሻ ሃሳብ ውድቅ መደረጉ ተገለፀ

ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ያቀረበችው የመነሻ ሃሳብ(ፕሮፖዛል) ውድቅ መደረጉን በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አማካሪ አቶ ተፈራ በየነ ገልፀዋል፡፡

አማካሪው እንዳሉት ግብፅ ሀምሌ 25፣ 2011 ዓ.ም ለኢትዮጵያና ሱዳን የግድቡ የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅን እንዲሁም ቀጣይ ቅንጅታዊ አሰራርን በተመለከተ አዲስ የመነሻ ሃሳብ(ፕሮፖዛል) ልካ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

ፕሮፖዛሉ ውድቅ የተደረገው ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትን ጥቅም የማያሥጠብቅ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

የግብፅ ወገን ላለመስማማት ተስማምቶ የመጣ ነው የሚመስለው ያሉት አማካሪው፤ ግብፅ ያቀረበችው ፕሮፖዛል የሶስትዮሽ ምክክር አሰራሩን የጣሰ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ግብፅ የአባይ ተፈጥሯዊ ፍሰት ሳይዛባ እንዲቀጥል ጠይቃለች ፣ ይህ ደግሞ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የልማት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሄራዊ አሰተባባሪ ም/ቤት ፅ/ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍቅርተ ታምር ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ በ2011 ዓ.ም 970 ሚሊየን ብር መገኘቱን ገልፀዋል፡፡

እስካለፈው ሰኔ መጨረሻ ድረስ በአጠቃላይ ከህብረተሰቡ ለግንባታው 12 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ድጋፍ መደረጉንም ነው ያስታወቁት፡፡

የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ የፕሮጀክቱን አሁናዊ ሁኔታ በተመለከተ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ውይይት ላይ ለተገኙ ተሳታፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም የኮርቻ ግድብ(ሳድል ዳም) 96 በመቶ፣የሃይል ማመንጫዎች 69 በመቶ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው 25 በመቶ፣ የሲቪል ስራው 84 በመቶ መጠናቀቃቸውን ገልፀዋል፡፡

በአጠቃላይ የፕሮጀክት አፈፃፀም ደግሞ 68 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን አብራርተዋል፡፡

እስካሁን ለግድኑ ግንባታ 99 ቢሊየን ብር ወጪ ሲደረግ፣ ፕሮጀክቱን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅም ተጨማሪ 40 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም ግድቡ የመጀመሪያው ምዕራፍ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት እንደሚጀምርም ነው የገለፁት፡፡