አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከደቡብ ሱዳን አቻቸው አወት ዴንግ አኩይል ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አወት ዴንግ አኩይልን ዛሬ በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሚኒስትሮቹ በነበራቸው ውይይት የደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደት ያለበትን ደረጃና ወደ ፊት ማስቀጠል በሚቻልበት ዙሪያ መክረዋል።

በደቡብ ሱዳን በኢጋድ አደራዳሪነት በተደረሰው ስምምነት መሰረት በአገሪቱ ያለው ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መሄዱን አድንቀዋል።

በስምምነት በተደረሰው የጊዜ ሰሌዳ መሰረትም ቀሪ ጉዳዮችን ወደ ተግባር ለማስገባት በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ሁለቱ ሚኒስትሮች ከመግባባት መድረሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።