የኢትዮጵያ እና የብሪታኒያ ደህንነት በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከል ተስማሙ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የብሪታኒያ ዓለም አቀፍ የደህንነት አገልግሎት በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከል ተስማሙ

የብሪታኒያ ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ በአፍሪካ ቀንድ እያደገ የመጣውን ሽብርተኝነት ከብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በቅንጅት ለመከላከል ተስማማ፡፡

ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ከእንግሊዙ ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ ኃላፊ ሰር አሌክስ ያንገር ጋር በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ባለው ወቅታዊ የፀጥታና የሽብርተኝነት ስጋት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

ኮሚሽነር ደመላሽ ከሀላፊው ጋር ባደረጉት ዉይይት በአፍሪካ ቀንድ የሽብር እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉትን የአልሸባብና የአይኤስ የሽብር ቡድኖች እንቅስቃሴን ለመግታት ሁለቱ ሀገራት የጀመሩትን የመረጃ ልውውጥ አጠናክረው በመቀጠል በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋለውን የሽብርተኝነት አደጋ ለመከላከል በጋራ እንደሚሰሩ መግባባት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በሰው ኃይል፣ በአደረጃጀት፣ በአሰራርና በቴክኖሎጂ ራሱን ለማጠናከር የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነር ደመላሽ፤ ተቋሙ ተልእኮውን በተሻለ መንገድ ለመፈፀም የሚያስቸለውን አመቺ የሆኑ የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን ለኃላፊው አብራርተውላቸዋል፡፡

የእንግሊዙ ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ በመረጃና ደህንነት ዘርፍ ያለውን የዳበረ ልምድ ለኢትዮጵያው አቻ ተቋም ለማካፈል ስምምነት ላይ የተደረሰ መሆኑን በመግለጽ፤ ይህ ሁለቱም በአካባቢው ያለውን የሽብር አደጋና አለመረጋጋት በጋራ ለመከላከል ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ኮሚሽነር ደመላሽ ገልጸዋል፡፡

የሁለቱ አገራት የመረጃና ደህንነት ተቋማት የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው የጠቀሱት ዳይሬክተር ጄነራል ኮሚሽነር ደመላሽ፤ ይህን የቆየ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ መግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል፡፡

የእንግሊዙ ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ ኃላፊ ሰር አሌክስ ያንገር በበኩላቸው በሁለቱ አገራት የፀጥታና የደህንነት የጋራ ጉዳዮች እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ዙሪያ ከዳይሬክተር ጄነራሉ ጋር ውይይት መደረጉን ገልፀው፤ በቀጣይ የፀረ-ሽብር እንቅስቃሴን በተመለከተ ስለሚኖራቸው የጋራ ትብብር መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ሰር አሌክስ ያንገር በቅርቡ ኢትዮጵያ በሽብርተኞች ላይ የወሰደቸውን እርምጃ አድንቀው፤ ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት እያካሄደ ያለው ሪፎርም ትልቅ የለውጥ እርምጃ በመሆኑ በቀጣይ ተቋማቸው ለአገልግሎቱ የአቅም ግንባታና የተሞክሮ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ (ምንጭ፡- ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት)