12ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን በጥቅምት 3 እንደሚከበር ተገለጸ

12ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ “ሰንደቅ አላማችን የብዝሀነታችን ድምር ውጤትና የአንድነታችን ምሰሶ ነው” በሚል መሪ ቃል ጥቅምት 3 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚከበር ተገለጸ፡፡

ቀኑ ሲከበር መንግስት የሚተገብራቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር እንቅስቃሴዎች፣ ስለ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች፣ ስለ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና በፌዴራል ስርዓቱ ውስጥ ስለህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት የጋራ መግባባት በሚፈጥር መልኩ በመወያየት እንደሚሆንም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

በሕገ-መንግሥቱም ሆነ በአዋጆች ዕውቅና ያገኘውን ሰንደቅ ዓላማ ማክበርና በጋራ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ ተገቢ እንደሆነም ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሰንደቅ ዓላማ የአገራችን ሉዓላዊነትና የሕዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት መገለጫ ነው፡፡ (ምንጭ፡-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት)