የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ከዳር ለማድረስ አሜሪካ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል አሜሪካ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በዴቪድ ፕራይስ የተመራውን የአሜሪካ ልዑካን ቡድን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ለልዑካን ቡድኑ በሀገሪቷ የተከናወኑ ቁልፍ የለውጥ ስራዎችን አስመልክቶ ገለጻ ተድርጎለታል፡፡

የፊታችን ግንቦት 2012 ዓ.ም የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን ሲሉም የልዑካን ቡድን መሪው ተናግረዋል፡፡

የተጀመረውን ለውጥ በአግባቡ ለማስተዳደር መንግስት ከፍተኛ የሆነ ህዝባዊ ተሳትፎን ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ነው አቶ ታገሰ ለልዑካን ቡድኑ የተናገሩት፡፡

ምክር ቤቱ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ጥያቄዎች ለማስተናገድና ለመፍታት በምክር ቤቱ በርካታ የለውጥ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሀገራዊ ለውጡን በዘላቂነት ለማስቀጠል የአሜሪካ ኤምባሲ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ሲሆን፣ ኤምባሲው እያደረገው ላለው ጥረት አፈ- ጉባኤው አመስግነዋል፡፡

(ምንጭ፡-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት)