በጠ/ሚ ዐብይ አህመድ የተጻፈው “መደመር” መጽሐፍ ቅዳሜ ይመረቃል

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አማካኝነት በመደመር እሳቤ ላይ የተጻፈው መጽሀፍ የፊታችን ቀዳሜ ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚመረቅ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገልፀዋል።

አቶ ንጉሱ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የመደመር እሳቤን በተመለከተ የተጻፈው መጽሀፍ በአማርኛ፣ በአፋን-ኦሮሞ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች የተጸፈ ነው።

የመፅሃፉ ምረቃም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ አዲስ አበባን ጨምሮ በ20 ከተሞች በአንድ ቀን የሚከናወንም ይሆናል።

በዋናነትም በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ጅማ፣ ባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ ጋምቤላ፣ አሶሳ፣ ጅግጅጋ፣ ሰመራ እና ሀረር ከተሞች ይመረቃል። በውጭ አገርም በተወሰኑ ከተሞች በተለይም በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ሚኒሶታ እና ናይሮቢ የምረቃ ስነ ስርዓቱ የሚከናወን መሆኑ ተገልጿል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይም የየከተሞቹ ነዋሪዎች፣ ባለስልጣናት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሴቶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። መሰናዶዉም የአካባቢውን ባህላዊ ይዘት በያዘ መልኩ እንሚከናወን ነው የገለፁት፡፡

እንደ አቶ ንጉሱ ማብራሪያ መጽሀፉ በ1 ሚሊየን ኮፒ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ህትመቱ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ማተሚያ ቤቶች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ታትሟል። የኢንግሊዘኛው ቅጂ ግን ከሶስት ወራት በኋላ እንደሚደርስ አስታውቀዋል።

መጽሀፉ በአሁኑ ወቅት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የተሰራጨ ሲሆን፤ በቀጣይም በተለያዩ የዓለም ሀገራት ለሽያጭ እንደሚቀርብ ተጠቁሟል።

የአንዱ መጽሀፍ ዋጋ 300 ብር (ሶስት መቶ ብር) ሲሆን ከመጽሀፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በአገሪቱ ትምህርት ቤቶችን ለማስገንባት ይውላል።