ም/ጠ/ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከጣሊያን የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ

የኢትዮጵያ ም/ጠ/ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጣሊያን የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በሮም በሚካሄደው የኢትዮ ጣሊያን የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሓላፊዎችና የንግዱ ማህበረሰብ ልዑካን ቡድንን በመምራት ጣሊያን ተገኝተዋል፡፡

በዚህም ሀገራቱ ያላቸውን ዲፕሎማሲና የልማት ትብብሮቻቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከጣሊያን ሴኔት ፕሬዝዳንት ማሪያ ኤልዛቤታ አልበርቲ ጋር በሮም ተወያይተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በተለይም ከኤርትራ ጋር የቆየውን የሻከረ ግንኙነት የተሻለ ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የተጫወቱት ሚና ለሌሎች ሀገራት በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ የ2019ኙን የዓለም የኖቤል ሽልማት በማሸነፋቸው ለኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክም አስተላልፈዋል፡፡

ጣሊያንና ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ አብረው በጋራ እንደሚሰሩም በነበረው ውይይት ላይ ተነስቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅት ፋኦ ዋና ዳይሬክተር ጄነራል ኩን ዶንግ ዩን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅትም ዓለም አቀፉ የምግብና የእርሻ ድርጅት ፋኦ በኢትዮጵያ ያለውን የለውጥ ሂደትና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎችን እንደሚደግፍ ነው ያረጋገጡት፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ዛሬ በሚከፈተው የኢትዮ ጣሊያን የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ተገኝተው ፣ከተለያዩ ተቋማት መሪች ጋርም ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል፡፡