በሀገራችን 160 ወባማ ወረዳዎች ርጭት እየተካሄደ ነው

በሀገራችን 160 ወባማ ወረዳዎች ላይ ክረምትን ተከትሎ ሊከሰት ከሚችለው የወባ በሽታ ወረርሽኝ ለመከላከል ርጭት እያካሄደ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ ።

የሚኒስቴር መስሪያቤቱ የወባ ፕሮግራም ኦፊሰር አቶ ደረጀ ድሉ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት ፤ በሀገራችን በሚገኙ 160 ወባማ ወረዳዎች ላይ ርጭት ለማካሄድ ከ916 ሺ ኪሎ ግራም በላይ ጸረ ወባ መድሃኒት ከነመርጫ መሳሪያዎች ጋር ተጓጉዘዋል ።

ከነሐሴ ወር ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የስራ ዘመቻ በ5 ሚሊየን ቤቶች ላይ የጸረ ወባ መድሐኒት ርጭት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

 በዚሁ የመከላከል ስራም 25 ሚሊየን ህዝብ ከወባ በሽታ መጠበቅ እንደሚቻል ጠቁመዋል ።

በተጨማሪም በወባማ ወረዳዎቹ ከዓምና ጀምሮ እስካሁን 24 ሚሊየን የአልጋ አጎበሮች ለህብረተሰቡ  መታደሉን አስታውቀዋል ።

ከዚሁም ውስጥ ከ300 ሺ በላይ የአልጋ አጎበሮች የአየር መዛባቱን ተከትሎ በአገራችን የተለያዩ አከባቢዎች ላይ የጎርፍ አደጋ ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መሰራጨቱን አመልክተዋል።

በወባማ ወረዳዎች ላይ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የወባ በሽታ መድሃኒት እንዲያገኙ በሁሉም የህክምና ተቋሞች በቂ መድሃኒት መላኩንና አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በክልሎች ያሉት የህክምና ባለሞያዎችና የአንድ ለአምስት የህዝብ ንቅናቄ በመጠቀም በሽታውን የመከላከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ደረጀ አመልክተዋል ።

ህብረተሰቡ የአከባቢውን ንጽህና በመጠበቅ የተሰጡትን የአልጋ አጎበሮችን በአግባቡ እንዲጠቀም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።