ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቀጣዩ ዓመት ተጨማሪ ተማሪዎችን ይቀበላል

ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቅበላ አቅሙን ለማሳደግ እንዲረዳው በሚከፍታቸው ሁለት አዳዲስ ካምፓሶች ተጨማሪ ተማሪዎችን እንደሚቀበል ለዋልታ ገለፀ፡፡

ሁለቱ አዳዲስ ካምፓሶች ሠላምና ሜዲካል እንደሚባሉ በዩኒቨርሲቲው በስትራቴጂክ ማኔጅመንትና ኮሙኒኬሽን ክፍል የድረ ገፅና የማህበራዊ ሚዲያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሙሉ ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

በሠላም ካምፓስ የጨርቃ ጨርቅ ትምህርት፣በሜዲካል ካምፓስ ደግሞ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገንብቶ የህክምና ትምህርት እንደሚሰጥ ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው በመደበኛ፣ በማታ፣በርቀትና በድህረ ምረቃ መርሃ ግብር 52 ሺ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ አቶ ሰለሞን ገልፀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በአዲሱ ዓመት በመደበኛ መርሀ ግብር አንድ ሺ ተጨማሪ ተማሪዎችን በመቀበል የቅበላ አቅሙን 14ሺ እንደሚያደርስ ነው በገለፃው የተመለከተው፡፡

ዩኒቨርሲቲው በቅድመ ምረቃና ድህረ ምረቃ መርሀ ግብር 68 የተለያዩ የትምህርት ዘርፎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ በድህረ ምረቃ መርህ ግብርና ለማህበረሰብ አገልግሎት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚንቀሳቀስም ለማወቅ ተችሏል፡፡

‹‹የድህረ ምረቃ መርህ ግብር ዘርፍን ለማስፋፋትና ለማጠናከር ከውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅትና በአጋርነት እየሰራን ነው›› ብለዋል-አቶ ሰለሞን፡፡

ዩኒቨርሲቲው እያካሄደ ባለው የማስፋፊያ ሥራ መምህራን ጥቅማቸው ተከብሮላቸው ሙሉ አቅማቸውን ለማማር ማስተማሩ ሂደት ያውሉ ዘንድ የመኖሪያ ቤት እየተገነባ መሆኑንም አቶ ሰለሞን አስገንዝበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የማህበረሰብ ልማቶችን እያካሄደ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሰለሞን አብዛኛውን ማህበረሰብ ያቀፈ ሥራ ለማከናወን ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ ከህዝቡ ጋርም 200 የማህበረሰብ ልማቶችን ለማከናወን ስምምነቶችን ተፈራርሟል ብለዋል፡፡

ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ1993 ዓ.ም ባህር ዳር ፖሊቴክኒክና ባህር ዳር የመምህራን ኮሌጅን በማጣመር ነው የተቋቋመው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንዱ ነው፡፡

የተሻሻሉ የቲማቲም ዝርያዎችን ማስተዋወቅ፣ የባዮ ጋዝ ልማት፣የህግ አገልግሎትና የአማርኛ ቋንቋን የማበልፀግ ሥራዎች ዩኒቨርሲቲው ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ ከሚሰራባቸው ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡