የኢድ አል አደሀ አረፋ በዓል በድምቀት ተከበረ

አንድ  ሺህ አራት መቶ ሰላሳ ሰባተኛው  የኢድ አል አደሀ አረፋ በዓል በመላው አገሪቱ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ተከበረ።

በአዲስ አበባ ስታዲየም የእምነቱ ተከታዮች እና መሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በድምቀት መከበሩ በስፍራው የተገኘው ሪፖርተራችን ዘግቧል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሀጂ መሀመድ አሚን ጀማል በሰጡት መግለጫ፥ መላው የእስልምና እምነት ተከታይ የኢድ አል አድሀ አረፋ በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና እርስ በእርስ በመተጋገዝ መሆን እንዳተለበት ገልፀዋል።

ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም የተመመው የበዓሉ ተሳታፊም ሶላት በማከናወን ለፈጣሪው  ምስጋና አቅርቧል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም የታደሙ የእስልምና እምነት ተከታዮች፥ የዘንድሮው በዓል ከአዲስ ዓመት መጀመሪያ ጋር መገጣጠሙ ልዩ መንፈስ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

ሀገሪቱ በጀመረችው የለውጥ ጉዞ ሙስሊሙ የድርሻውን እየተወጣ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ፥ ይህን ድርሻውን በአዲሱ ዓመት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

በመቻቻል፣ በመተባበርና መደጋፍ ላይ የተሰረተው አንድነታችን አንዲጠናከርም የበለጠ እንሰራለን ብለዋል።