አገር ዓቀፍ የትምህርት ውይይትና ስልጠና ነገ ይጀመራል

የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በሚረዱና ከዘርፉ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከትምህርት ማህበረሰቡ ጋር የሚደረገው አገር ዓቀፍ ውይይትና ስልጠና ነገ እንደሚጀመር ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ዛሬ በተሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ውይይትና ስልጠናው በመማር ማስተማሩ ሂደት ዙሪያ የሚስተዋሉ ድክመቶችና ጥንካሬዎች ተፈትሸው በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያግዙ ግብዓቶች ይሰበሰባሉ፡፡

ባለፉት ዓመታት በአገር ዓቀፍ ደረጃ ከትምህርት ማህበረሰቡ ጋር በተደረጉት ውይይቶችና ምክክሮች እጅግ በጣም ጠቃሚ ሀሳቦችና ልምዶች መገኘታቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ስልጠናና ውይይትም የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሳደግ የሚረዱ ግብዓቶች እንደሚገኙ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በሁለትዮሽ ግንኙነት ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን በነፃነት የሚያንሸረሽሩበት መድረክ እንደሚሆንም አስገንዝበዋል፡፡

የአሁኑ ስልጠናና ውይይት ወላጆችን የሚያሳትፍ መሆኑ ከሌላው ጊዜ የተለየ እንደሚደርገው አቶ ሽፈራው ጠቁመው ፤ይህም የዋናውን ባለድርሻ አካል ሃሳብ ለመካፈልና አስተያየቱን ለማድመጥ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

አቶ ሽፈራው እንዳሉት ለውይይቱ ሶስት ዋና ዋና አጀንዳዎች ተመርጠዋል፡፡

እነዚህም ባለፉት 25 ዓመታት በተመዘገቡት ውጤቶች የትምህርት ዘርፍ ሚናና የአገሪቱ ዕድገት፤ህብረብሔራዊነትን በማጠናከር መልካም ዕሴቶችን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እና በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ በሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርቶች የተገኙ ውጤቶችና ድክመቶችን መፈተሸ መሆናቸውን አመልክተዋል ፡፡

በውይይቱ የተዛቡ አመለካከቶች ተወግደው ብቁ፣ በዕውቀት የበለፀገ፣ለአገሩና ለወገኑ የሚወግንና ለለውጥ የሚተጋ ትውልድ ለማፍራት ይሰራል ብለዋል-ሚኒስትሩ፡፡

ተማሪን ማዕከል ያደረገውን የመማር ማስተማር ሂደት ጉድለቶቹን በመፈተሸና ጥንካሬዎቹን በማጉላት ለተሻለ ለውጥ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል፡፡

ውይይቶቹ በተለያዩ ደረጃዎች የሚካሄዱ ሲሆን የመምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ከነገ ጀምሮ ለቀጣዮቹ ስምንት ቀናት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል ፡፡

የተማሪዎች ውይይት ከመስከረም 17 በኋላ እንደየትምህርቤቶቹ ዝግጅት ከሶስት እስከ ስምንት ቀናት በሚቆይ ጊዜ ይካሄዳል ነው ያሉት፡፡

‹‹በአንዳንድ አካላት ተማሪዎች ከክልላቸው ውጭ እንዳይሄዱ ቅስቀሳ እየተደረገ ነው፤ በዚህም ወላጆች በፍራቻ ተውጠዋል›› በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ሽፈራው ‹‹የሚናፈሰው ወሬ ከእውነታው እጅጉን የራቀና የተሰሳተ ነው ብለዋል››፡፡

በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የችግሩ ሰለባ የሆኑበት አጋጣሚ አለመኖሩን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

ህብረተሰቡም ከዚህ ዓይነት አሉባልታ ራሱን በማራቅ ለዘመናት ተቻችለውና ተፋቅረው የኖሩበትን አኩሪ ባህል በማደስ ጉዞዋቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ሚኒስትሩ ማሳሰባቸውን ዋልታ ዘግቧል ፡፡