ኮሚሽኑ የጎርፍ አደጋ እንደቀነሰ በጥናት መረጋገጡን አስታወቀ

ብሔራዊ የአደጋ ስጋትና መከላከል አስተዳደር ኮሚሽን በሀገሪቱ በተደረገው የመከላከል ስራ የጎርፍ አደጋ መቀነሱን አስታወቀ ፡፡

ባሳለፍነው ክረምት በመላ አገሪቱ ካሉት 700 የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ወረዳዎች ውስጥ በ300ዎቹ በተካሄደው ጥናት የጎርፍ አደጋ መቀነስ መቻሉን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ደበበ ዘውዱ ለዋልታ አስታውቋል ፡፡

በዚሁም መሰረት በመላ ሀገሪቱ ግማሽ ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብ ከቀያቸው ሊፈናቀሉ ይችላሉ ተብሎ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም፤ በደረሰው የጎርፍ አደጋ 125 ሺ ህዝብ ብቻ ከቦታው ሊፈነቀል መቻሉን አረጋግጠዋል ፡፡

ጥናቱ እንደሚያሳየው ግን አስቀድሞ የመከላከል ስራ ባይከናወን ኖሮ አደጋው የከፋ ይሆን እንደነበር አመልክተዋል ፡፡

በአዲሱ ዓመት ደግሞ አደጋውን ይበልጥ ለመከላክል በተፋሰሶች የሚደረገው ጥናት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ፡፡

ኮሚሽኑ በአማራ ፣በዓፋር፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሊ በጎርፍ አደጋው የተፈናቀሉትን 220 ሺ ኩንታል ምግብና ሌሎች 170 ሺ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ ወረዳዎች ላይ የሚኖሮው ህዝብ የጎርፍ አደጋውን ለመቀነስ በሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎች እንዲሳተፍ መደረጉን አስረድተዋል ፡፡

ባለፈው ዓመት በጎርፍ አደጋ መከላከያዎችና በእርሻ ማሳዎች ላይ 200 አደጋዎች መከሰታቸውን ጠቁመዋል ፡፡

ኮሚሽኑ በሀገራችን ኢልኒኖ ባስከተለው የአየር ለውጥ ሳቢያ ከ10 ሚሊየን በላይ ህዝብ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ከመዳረጉም ባሻገር ፤ህዝቡ ለተለያዩ ችግሮችና ለከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ይጋለጣል የሚል ስጋት እንደነበር አብራርተዋል ፡፡

ስለሆነም አገሪቱ ለተረጂዎቹ አፋጣኝ እርዳታ ለመስጠት እንዲቻል 4 ሚሊየን 6ሺ ኩንታል እህል በመጠባበቂያነት መያዙን አመልክተዋል ፡፡

ከአምስት ወራት በፊት መንግስት ድርቁን ለመቋቋም እንዲቻል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ 1ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ለተረጂዎች እንዲለግስ ጥሪ አቅርቦ እስካሁን 800 ሚሊየን ዲላር ማግኘት መቻሉን አቶ ደበበ አስታውቀዋል ፡፡