መምህራን በትምህርት ጥራትና በወቅታዊ ጉዳይ እየተወያዩ ነው

በአራተኛው አገር አቀፍ መድረክ የአዲስ አበባ ከተማ መምህራን በትምህርት ጥራትና በወቅታዊ ጉዳይ ውይይት ከትናንት አንስቶ እያካሄዱ መሆናቸው ተመለከተ ፡፡

በዚሁ ለአስር ቀናት በሚቆየው ውይይት በቂርቆስና በአራዳ ክፍለ ከተሞች ከ4ሺ በላይ መምህራን ውስጥ በአብዮት ቅርስ እና በጥርቁር አንበሳ ትምህርትቤቶች እየተወያዩ  ይገኛሉ ፡፡

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽሕፈትቤት ኃላፊ አቶ አዳነ ሱሌ ለዋልታ እንደገለጹት ፤የውይይቱ  ዓላማ መምህራን ብቁ ምርታማና በስነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራት በሚያረጉት ጥረት ግንዛቤያቸውን ለማዳበር ያለመ ነው ፡፡

መምህራን በሀገራችን ባለፉት 25 ዓመታት የተመዘገቡ ውጤቶችና ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች በተመለከተ የተሻለ ግንዛቤ አግኝተው ለተማሪዎቻቸውም በትምህርት ሂደት ላይ ለማስረጽ የሚያስችላቸው መሆኑን አስገንዝበዋል ፡፡

የውይይቱ ዋንኛ ነጥብ ደግሞ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚያተኩርም አስታውቀዋል ፡፡

በዚሁ ውይይት ላይ ከክፍለ ከተማው የተውጣጡ 4ሺ 400 መምህራን ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቁመዋል ፡፡

ከተሳታፊዎች ውስጥ  መምህር ሽመልስ እልፉ እና ማሚት ሃለፎም በሰጡት አስተያየት ስልጠናው የትምህርት ፖለሲ በማወቅ የተሻለ ስራ በመስራት ራኢ ያለው ዜጋ ለማፍራት እንደሚረዳቸው ገልጸዋል ፡፡

ውይይቱ በመማር ማስተማሩ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች በአግባቡ በመፍታት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስፈን ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አስረድተዋል ፡፡

ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በከተማው ከ50ሺ በላይ መምህራን እየተሳተፉ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል ፡፡