የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በመጠናቀቅ ላይ ነው

የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 87 በመቶ መጠናቀቁን የውሃ ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

 

የሚኒስቴር መስሪያቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደገለጹት ፤

በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የቆሻሻ ማጠራቀምያ ቦታ ላይ የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ በ118 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ::

 

የፕሮጀክቱ ግንባታ እስካሁን ድረስ 87 በመቶ የደረሰ ሲሆን፡ በታህሳስ ወር 2009 ዓመተ ምህረት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል ፡፡
 

ፕሮጀክቱን የሚገነባው መሠረቱን ዩናይትድ ኪንግ ደም ያደረገው የኮምቢሪጁ ኢንዱስትሪ ጋር በተፈረመ ስምምነት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

 

ፕሮጀክቱ 50 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችል ሲሆን፤ በዓመት 35 ሺ ቶን ቆሻሻ ጥቅም ላይ ያውላል ብለዋል ፡፡ 
 

በዚሁም የካርበንዳይኦክሳይድ ልቀትን በመቀነስ ረገድ በአካባቢ ጥበቃ ላይ አወንታዊ የሆነ ተፅዕኖ ይኖረዋል ነው ያሉት ፡፡

 

ከአዲስ አበባ ከተማ የሚወጣውን ቆሻሻ ጥቅም ላይ በማዋል በአካባቢ ላይ  እየደረሰ ያለውን የቆሻሻ መዝረክረክ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያስቀር አስረድተዋል፡፡

 

በዚህም ፕሮጀክቱ የከተማዋን ንጹህ ከመጠበቅም ባሻገር ለበርካታ ስራ አጦች የስራ ዕድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል፡፡

 

ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረው ረጲ ቆሻሻ መጣያ ስፍራ ከሰሃራ በረሃ በታች ካሉት አገሮች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ከቆሻሻ ሃይል ማመንጨት የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል ፡፡