ሚኒስትሩ ወጣቶች ተደራጅተው ከባንክ ብደር መጠቀም እንደሚችሉ አስታወቁ

መንግስት በከተማና በገጠር የሚገኙ ወጣቶች ከንግድና ከልማት ባንኮች የብድር አገልግሎት ለማግኘት የሚችሉበት አቅጣጫ ማስቀመጡን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አስታወቁ ፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን ዛሬ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስገነዘቡትየወጣቶች ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የሚጀምረው ከህገ መንግስቱ ነው ፡፡

መንግስትም ከፖለሲው ማውጣት ቀጥሎ አዲስ የወጣቶች ልማትና ተሳትፎ ስትራቴጂ ቀርጾ በዚህ ዓመት ስራ ላይ ማዋሉን አስታውቀዋል፡፡

ስትራቴጂውን ተከትሎ ደግሞ ባለፉት ዓመታት ሲገመገሙበት የነበረው የወጣቶች ልማትና ተሳትፎ የዕድገት ፓኬጅ እንደ አዲስ እንዲከለስ መደረጉን አመልክተዋል ፡፡

በሀገሪቱ አዳዲስ ለውጦች መጥተዋል ፣ኢኮኖሚው ሰፋ ብሎ አዳዲስ ገጽታዎችን መያዝ ጀምሯል ነው ያሉት ሚኒስትሩ ፡፡

ስለዚህ ወጣቶችን ሊጠቀሙባቸውና ሊሳተፉባቸው የሚችሉባቸው ገጽታዎች በጣም ከመበረከታቸው ጋር ተያይዞ ፍላጎታቸውም እያደገ በመምጣቱ ምክንያት አሰራር መሻሻሉን አብራርተዋል ፡፡

በተለይም በወጣቶች ዘንድ ቅሬታ ሲቀርብበት የነበረው የወጣቶች የብድር አገልግሎት በፍጠነት አለማቅረብ እና እስከ ገጠር አለመዝለቅ ችግር እንደነበር አንስተዋል ፡፡

አሁን ግን ችግሩን ለማስወገድ ልማት ባንክ ቅርንጫፎቹን ወደ ከተሞች፣ዞኖችና ወረዳዎች እንዲወርድ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ባንኩ ማሽነሪዎችን ከማቅረብ በተጨማሪ ለማኑፋክቸሪን የሚሆን ብድር የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡

በተለይም ንግድ ባንክ ለባለሃብት ብቻ ይሰጥ የነበረውን ብድር ለወጣቶች በአቅራቢያቸው የብድር አገልግሎት እንዲሰጥ መንግስት አቅጣጫ ማስቀመጡን ገልጸዋል ፡፡

ይህም ባንኩ ወጣቶች በንግድና በአገልግሎት ዘርፍ ተደራጅተው ለሚንቀሳቀሱ ወጣቶች የብድር አገልግሎቱ እንዲያገኙ መንግስት በወሰነው መሰረት በዚህ ዓመት ስራውን ይጀምራል ነው ያሉት፡፡

ከዚህም ሌላ የወጣት ማዕከላት ከዓላማቸው ውጪ ለስብሰባ ፣ለሰርግና ለሌላ ስራ ይወሉ የነበሩበትን አካሄድ በማቆም ወጣቱ መንፈሱን እያዝናና አዕምሮው የሚያጎለብትባቸው እንዲሆኑ እንደሚደረግ አስታውቀዋል ፡፡

ስለሆነም የፈደራል መንግስት ከክልሎች ጋር በመተባበር የወጣት ማዕከላቱ በበጀትና በግብኣት የሚጠናከሩበት፤ አዳዲስ ግንባታዎችም በሚስፋፉበት ጭምር ተወስኖ እየተሰራበት መሆኑን አስረድተዋል ፡፡