የ11 አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ሥራ በመጋቢት ወር ይጠናቀቃል

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግንባታቸው እየተከናወነ የሚገኙት የ 11 አዳዲስ  ዩኒቨርሰቲዎች  የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ሥራ በመጪው መጋቢት ወር እንደሚጠናቀቅ የትምህርት  ሚኒስቴር አስታወቀ ።  

በትምህርት ሚኒስቴር የ11 አዲስ ዩኒቨርስቲዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ለዋልታ እንደገለጹት በ2008 ዓም የዲዛይን ሥራቸው  ተጠናቆ  ባለፈው ግንቦት ወር ላይ ግንባታቸው የተጀመረው አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች በዘንድሮ የበጀት ዓመት መጋቢት ወር ላይ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታቸውን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ።

በ2009 ዓም መጋቢት ወር ላይ የ11 ዩኒቨርስቲዎች የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ሥራን በማጠናቀቅ እያንዳንዱ ዩኒቨርስቲ በ2010 ዓም 1ሺ500 ተማሪዎችን እንዲቀበል  እንደሚደረግ ዶክተር ሳሙኤል አስረድተዋል ።

አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎቹን ለመገንባት የተመረጡት አካባቢዎች የአገሪቱን የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት  ተደራሽነትንና ፍትሃዊነትን መሠረት ባደረገ መልኩ  መሆኑን ዶክተር ሳሙኤል አመልክተዋል።  

በአዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች ለመማርና ማሥተማር ሂደቱ የሚያገለግሉ የተለያዩ ህንጻዎችና መሠረተ ልማቶች  ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን የጠቆሙት  ዶክተር ሳሙኤል  በአጠቃላይ የዲዛይን እስከ ግንባታ ሥራዎችን ለማከናወን  በዘንድሮና ባለፈው ዓመት ከ3ነጥብ 2 ቢለዮን ብር በላይ ተመድቧል ብለዋል ።

የዩኒቨርሰቲዎቹን የግንባታ ሥራዎች ጥራታቸውንና ደረጃዎቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማስቻል የተሻለ ልምድ ያላቸውን የግንባታ ኮንትራክተሮችንና አማካሪዎችን መምረጥ  መቻሉንም  ዶክተር ሳሙኤል አክለው ገልጸዋል ።

እያንዳንዱ አዲስ ዩኒቨርስቲ ሙሉ ለሙሉ የግንባታና ማስፋፊያ ሥራዎቹ ሲጠናቀቁ  በአጠቃላይ  ከ10ሺ በላይ  ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው  ዶክተር  ሳሙኤል ተናግረዋል ።

የሁለተኛው  የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አካል የሆኑት  11 አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች የራያ ፣ ደባርቅ ፣እንጂባራ ፣መቅዳላ አምባ ፣ሰላሌ፣ አዳቡልቱ ፣ ደምቢዶሎ ፣ቦንጋ፣ወራቤ፣ ጂንካናቀብሪዳሃር  ዩኒቨርስቲዎች ናቸው ።