ቤተክርስቲያኗ በኢሬቻ በዓል ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች በፀሎት እያሰበች ነው

የኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በኢሬቻ በዓል አከባበር ሥነ ስረዓት ላይ በተፈጠረ ሁከት ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች በጸሎት እያሰበች ነው ፡፡

ቤተክርስቲያኗ በበዓሉ ሥነ ስርዓት ወቅት በደረሰው አደጋ የዜጎች ሕይወት በመጥፋቱ የተሰማትን ጥልቅ ሐዘንም ገለጸች፡፡

በቤተ ክርስቲያኗ ቋሚ ሲኖዶስ ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለጸው፤ በተከሰተው ሁከት ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖች ከዛሬ ጀምሮ ለሰባት ተከታታይ ቀናት  በጸሎት እንዲታሰቡ ተወስኗል፡፡

"ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ወገኖቻችን እግዚአብሔር እረፍተ ነፍስን እንዲሰጥልን ለሰባት ቀናት በጸሎት እንዲታሰቡ ቋሚ ሲኖዶስ ተስማምቷል" ሲል መግለጫው ያትታል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትሪያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘ ኢትዮጵያ እንደገለጹት፤  ፀሎተ ምሕላው በመላ ሀገሪቷ፣ በውጭ ሀገሮች በሚገኙ አህገረ ስብከቶችና ገዳማት፣ አድባራትና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ይደረጋል፡፡

ቤተክርስቲያኗ እግዚያብሔር ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ሰላምን እንዲሰጥ፣ በችግሩ ምክንያት ተጎድተው በሕክምና ላይ የሚገኙ ወገኖች ጤናና ፈውስ እንዲያገኙ ጸሎተ ምህላውን እንደምታደርግ ነው የገለጹት፡፡

''በሀገሪቷ ውስጥ ጥያቄ ያላቸውና ምላሽ የማፈልጉ ዜጎች ጥያቄዎቻቸውንና ፍላጎታቸውን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ለመንግስት እንዲያቀርቡ፣ መንግስትም ባለበት አገራዊ ኃላፊነት መሰረት ጥያቄዎችን በአግባቡ እየተቀበለ ፍትሐዊ ምላሽ እንዲሰጥባቸው ቤተክርስቲያኗ ታሳስባለች'' ብለዋል፡፡

በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኢሬቻ በዓል ሥነ ስርዓት ላይ በደረሰው አደጋ የተሰማትን ጥልቅ ሐዘን ገልፃለች።

ቤተክርስቲያኗ በአደጋው ለሞቱ ሰዎችም እግዚአብሔር በመንግስቱ እንዲቀበላቸው እንደምትፀልይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከችው መግለጫ ጠቁማ፤ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እንደምትመኝ አስታውቃለች- (ኢ ዜ አ /፡፡