የጤናው ዘርፍ በምርምር መደገፉ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ረድቷል

የጤናው ዘርፍ በምርምርና ጥናቶች በደንብ እንዲደገፍ መደረጉ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ አስችሏል፡፡

ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከልና የመግታት ጥረቱ በጥናትና ምርምር መደገፉ ትልቅ እመርታ ማምጣቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ ትናንት የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሶስተኛ ሀገራዊ የሳይንስ ጉባዔ በኢንስቲትዩቱ አዳራሽ ሲጀመር እንደተናገሩት በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ መሻሻልና ለውጥን ያመጡ ምርምሮች ተካሂደዋል፡፡

በጤናው ዘርፍ የሚካሄዱት ጥናቶችና ምርምሮች ለሚመለከታቸው አካለት እየቀረቡ በግብዓትነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንደሚደረጉም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡ በዘርፉ የሚተላለፉ ውሳኔዎችም መረጃዎችን መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱን ጨምሮ የምርምርና የሥልጠና ማዕከላትን የማጠናከር፣ ቤተ ሙከራዎችን  የማስፋፋት ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆናቸውን ዶክተር ከሰተብርሃን ገልፀዋል፡፡

የእናቶችና ህፃናት ሞት መቀነስ፣የኤች አይቪ/ ኤድስ ስርጭትን መከላከል፣ እንዲሁም በቅርቡ ተከስቶ የነበረውን የአተት በሽታን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡

የሀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አምሀ ከበደ በበኩላቸው  ኢንስቲትዩቱ ለህብረተሰብ ጤና መከላከልና ለሥነ ምግብ ችግሮች የሚረዱ የተለያዩ ምርምሮችን በማውጣት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረጉን ይናገራሉ፡፡

የምርምር ውጤቶቹም ለሚመለከታቸው አካላት በተለያዩ መንገዶች እንዲደርሱ ሲሰራ መቆየቱን ነው ዶክተር አምሀ የገለፁት፡፡ በአሁኑ ጉባዔም ህብረተሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ ከ150 በላይ የጥናት ውጤቶች እንደሚቀርቡ ጨምረው አስረድተዋል፡፡

የጥናት ውጤቶቹ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፣ ሥነ ምግብ፣ ባህላዊና ዘመናዊ ህክምና፣የህብረተሰብ ጤና ላቦራቶሪ አቅም ግንባታና ጥራትን ማራጋገጥ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ዶክተር አምሀ አስገንዝበዋል፡፡

‹‹መረጃ ላይ መሰረት ያደረገ ውሳኔ ለህብረተሰብ ጤና ለውጥ›› በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው ጉባዔ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፣ከጤና ማዕከላት፣ከአጋር ድርጅቶችና ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ  ከ500 በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ፡፡

ከኢንስቲትዩቱ የተገኙት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ቀደም ሲል በተካሄደው የኢንስቲትዩቱ ሁለተኛ አገራዊ ጉባዔ በተለያዩ መስኮች የተደረጉ 87 የምርምር ውጤቶች በቴክኒካል ሪፖርት መልክ ለተጠቃሚዎች እንዲደርሱ ተደርጓል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ 175 የጥናት ግኝቶች በታወቁ የሳይንስ ጆርናሎች የታተሙ ሲሆን በጤናው ዘርፍ ለፖሊሲ ውሳኔ የሚረዱ አምስት ያህል ፅሁፎችም ተዘጋጅተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና ምርምሮችን የማካሄድና የላቦራቶሪ አገልግሎት የመስጠት ተግባርን በዋናነት እንዲያከናውን የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡