ሁከቱ በቱሪስቶች ምንም ጉዳት እንዳላደረሰ ሚንስቴሩ አስታወቀ

በኢትዮጵያ ተከሰቶ በነበረው ሁከትና አለመረጋጋት በቱሪስቶች ላይ አንዳችም ጉዳት እንዳልደረሰ የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ የቱሪዝም ልማት ዘርፍ ሚንስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ታደለች ዳልቾ ትናንት ከሆቴል ባለሐብቶችና ሥራ አስኪያጆች ጋር ባደረጉት የምክክር መድረክ በቅርቡ በሀገሪቱ የነበረውን ሁከትና ግጭት ተከትሎ በቱሪስቶች ላይ የንብረት፣ አካል ወይም የሕይወት ጉዳት እንዳልደረሰ ገልጸዋል፡፡

ይሁንና ወይዘሮ ታደለች እንደገለጹት፤ በሆቴሎችና ሎጆች ላይ ከፍተኛ የንብረት መውደም ከመድረሱም ባሻገር በቱሪዝም ኢንዱስትሪው መቀዛቀዝ መታየቱን ገልጸዋል፡፡

የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ኢንደስትሪ ለማነቃቃት እንዲቻል ከአስጎብኝዎች፣ የሆቴሎች ማሕበርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተውጣጣ ንዑስ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡

በሆቴሎች፣ ሪዞርቶችና ሎጆች ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ባለሐብቶቹ የደረሰባቸውን ጉዳት በተደራጀ መልኩ መረጃው ለኮማንድ ፖስቱ ቢያቀርቡ መረጃዎቹ ተለይተውና ተተንትነው ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን መፍትሄ ለመሻት ጥረት እንሚደርግም አስታውቀዋል፡፡

የቱሪዝም ኢንደስትሪውን ወደነበረበት ለመመለስ እንዲቻል ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ሰላምን በማስከበር በኩል የድርሻውን እንዲወጣ ሚንስቴሩ ጥሪውን አቅርቧል፡፡፡

የውይይቱ ተሳፊዎች በሁከትና ግርግሩ ሳቢያ የቱሪዝም ፍሰቱ በመቀነሱ ከፍተኛ የሆነ ገቢ እጥረት እንዳጋጠማቸው አመልክተዋል፡፡

ስለሆነም ባንኮች የብድር እፎይታ ጊዜ እንዲሰጧቸው መንግስት ሁኔታዎቹን እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡

አሁን በሀገሪቱ የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ቱሪስቶች እንዲያውቁት የመገናኛ ብዙኃንና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ከፍተኛ ሥራዎችን ማከናወን እንዳለባቸው አመልክተዋል ፡፡

የአዲስ አበባ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ነው በውይይቱ የተመለከተው ፡፡

አዲስ አበባ ከጄኔቫና ኒውዮርክ በመቀጠል ከፍተኛ የቱሪዝም የኮንፍረንስ መዳረሻ እንደሆነች የሚታወቅ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡