ኮሚሽኑ ለ9ነጥብ7 ሚሊየን ተረጂዎች ወርሃዊ ቀለብ ማደል መቀጠሉን አስታወቀ፡፡

በሀገሪቱ በድርቅ ምክንያት ለተጠቁ 9 ነጥብ 7 ሚሊየን ተረጂዎች ወርሃዊ ቀለብ እስከ ታህሳስ ወር ማደል እንደሚቀጥል የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበበ ዘውዴ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤በ1ሺ 900 ማደያ ጣቢያዎች አስቸኳያ ምግብ ለሚያስፈልጋቸው 9ነጥብ 7 ህዝብ የጥቅምት ወር 1 ነጥብ 45 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ተሰጥቷል ፡፡

መጀመሪያ በሀገራችን 10 ንጥብ 2 ሚሊየን ህዝብ ለድርቅ መጋለጡን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ፤በበልግ ወቅት በተደረገው ዳሰሳ ጥናት ግን የተረጂዎች ቁጥር ወደ 9 ነጥብ 7 ሚሊየን ዝቅ ማለቱን ነው ያመለከለቱት ፡፡

በመላ ሀገሪቱ ከባለፈው መጋቢት ወር አንስቶ ዝናብ እየዘነበ ጥሩ የምርት ተስፋ ቢኖርም ምርቱ እስከሚሰበሰብ ድረስ የሚሰጠው እርዳታ እስከ ታህሳስ 2009 ዓመተ ምህረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስረዱት ፡፡

ኮሚሽኑ ከታህሳስ በኋላ ደግሞ ተባባሪ ሆኖ በመቀጠል ሴክተር መስሪያቤቶችና ሌሎች የመንግስታቱ ህብረት ተወካዮች ፣ የሁለትዮሽ ስምምነት ያላቸው ለ21 ቀን ዳሰሳ ጥናት እንደሚያካሂዱ አስታውቀዋል ፡፡

በዚሁም የየክልሉ የዝናቡ ፣የሰብሉ ፣የእርሻ ፣የከብቶች፣ የመጠጥ ውሃና ፣የሰዎች ጤንነት  ሁኔታ ሁሉ እንደሚጠና አብራርተዋል ፡፡

ከዚህ ጥናት በኋላም የሚመጣው ውጤት በኢትዮጵያ ውስጥ  ምን ያህል ተረጂ እንደሚሆን በይፋ እንደሚገለጽ ነው ዳይሬክተሩያመለከቱት ፡፡

መንግስት፣መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣የዓለም ምግብ ፕሮግራም ድርጅት ባደረጉት ርብርቦሽ ከ16 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ጥቅም ላይ መዋሉን አቶ አበበ አንስተዋል ፡፡

በዚሁም በሀገሪቱ ካሉት ከ9 ሚሊየን በላይ ተረጂዎች ውስጥ መንግስት የ5 ነጥብ 7 ሚሊየን ህዝብ ህይወት በመታደግ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እንደነበረው አስታውቀዋል፡፡