የመዲናዋ የልማታዊ ሴፍቲኔትና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ ወረዳዎች ተለዩ

የአዲስ አበባ የመጀመሪያው ዙር የልማታዊ ሴፍቲኔትና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ ወረዳዎች መለየታቸው ተገለፀ።

ፕሮግራሙ በመዲናዋ 10 ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ወረዳዎች ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በጥናት ለይቶ በተለያዩ የስራ መስኮች በማሳተፍና የቀጥታ የምግብ ዋስትና ድጋፍ በመስጠት ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

በጥናቱ መሰረት ለዕጣ ከቀረቡት ወረዳዎች መካከል 35ቱ የመጀመሪያው ዙር ተጠቃሚ ሆነው የተመረጡ ሲሆን በፕሮግራሙ በከተማና አረንጓዴ ልማት ዘርፍ፣ በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና ማስወገድ፣ በከተማ ግብርናና መሰል ዘርፎች የስራ እድል ለመፍጠር ታስቧል።

በተጨማሪም መስራት ለማይችሉ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞችና ህፃናት የቀጥታ ድጋፍ በማድረግ የአጭር ጊዜ የምግብ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ጥረት እንደሚደረግ ተገልጿል።

ለፕሮግራሙ ማስፈፀሚያ 450 ሚሊዮን ዶላር የተበጀተ ሲሆን 150 ሚሊዮን ዶላር በመንግስትና ቀሪው 300 ሚሊዮን ከዓለም ባንክ የተገኘ ድጋፍ  ነው።

ከጠቅላላ በጀቱ 70 በመቶው ለአዲስ አበባ ቀሪው በሌሎች የክልል ከተሞች ተግባራዊ ይሆናልም ተብሏል።

የመዲናዋ ከንቲባ ድሪባ ኩማ እንደገለጹት ፕሮግራሙ ከድህነት ወለል በታች ያሉ ነዋሪዎችን ከመርዳትና ራሳቸውን እንዲችሉ ከማድረግ ባሻገር ፅዱና አረንጓዴ ከተማ ለመፍጠር ጉልህ ሚና ይኖረዋል።

ዕጣው ከሁሉም ክፍለ ከተሞች በጥናት የተለዩትን ወረዳዎች ያካተተ ሲሆን ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01፣ 11፣ 03 እና 09፤ ከየካ ወረዳ 02፣ 01፣ 06 እና 12፤ ከልደታ ወረዳ 04፣ 01፣ 02 እና 05፤ ከአራዳ ወረዳ 08፣ 01፣ 05 እና 03 ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05፣ 03፣ 08 እና 09 ዕጣ የወጣላቸው ናቸው።

በተጨማሪም ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03፣ 10፣ 01 እና 07 ከጉለሌ ወረዳ 04፣ 07፣ 01 እና 09 ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ 02፣ 05 እና 06 ከኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ 15፣ 11 እና 09 ከቦሌ ወረዳ 11 በዕጣው የተካተቱ ሲሆን በድምሩ 35 ወረዳዎች በአንደኛው ዙር የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

ፕሮግራሙ በወረዳዎቹ በዚህ ዓመት የሚጀምር ሲሆን ለሁለተኛው ዙር የልማታዊ ሴፍቲኔትና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም 55 ወረዳዎች የሚመረጡ ይሆናል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።