በዓለም የሚገኙ የማይዳሰሱ የባህላዊ ቅርሶች ላይ ጥበቃ ማድረግ ሊጠፉ የተቃረቡትን የማይዳሰሱ የባህላዊ ቅርሶችን በማቆየት ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት በ11ኛው የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባኤ ተመለከተ ።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ፣ የትምህርትና ባህል ድርጅት( ዩኔስኮ) የባህል ረዳት ዳይሬክተር ሚስተር ፍራንሲስኮ በተሠጠው መግለጫ ላይ እንደገለጹት የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ በመጥፋት ላይ ያሉትን የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለማዳን በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ መሳተፍና እውቅናም መሥጠት ይገባዋል ብለዋል ።
እንደ ሚስተር ፍራንሲስኮ ገለጻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዓለም ህዝቦች በግጭት፣ በተፈጥሮ አደጋና በግሎባላይዜሽን ምክንያት የማይዳሰሱ ቅርሶቻቸውን እያጡ በመሆናቸው ቅርሶቹን ጠብቆ የማቆየት እርምጃው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ።
በ11ኛው የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃ የበይነ መንግሥታት ኮሚቴ ጉባኤ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዮናስ ደስታ በበኩላቸው እንደገለጹት እንደዚህ አይነት በቅርሶች ላይ የሚካሄድ ጉባኤ የማይዳሰሱ ቅርሶችን ጠብቆ በማቆየት ረገድ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያስፈልጉትን የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ለማግኘት ትልቅ እግዛ እንደሚኖረው ገልጸዋል ።
የዓለም ግሎባላይዜሽን ሁኔታ በህዝቦች የማይዳሰሱ ቅርሶች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል ባለመሆኑ ምክንያት ከጉባኤው የመወያያ ርዕሶች እንዱ እንደሚሆን የገለጹት አቶ ደስታ አገራት የተሻለ የማይዳሰሱ ቅርሶች ላይ የሚኖራቸው ግንዛቤን ማሳደግና የቅርሶችን አስተዳደር ማሻሻል የመፍትሄ አቅጣጫዎቹ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል ።
በ11ኛው የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባኤ ጸሃፊ የሆኑት ሚስተር ቲም ኩርቲስ በበኩላቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች ከህዝቦች ማንነት ፣ ባህልና አኗኗር ዘይቤ ጋር የተቆራኙ መሆናቸውን በመጠቆም የትኛውም መንግሥት ፣ ማህበረሰብና ህዝብ በአገዳ ላይ የሚገኙ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶችን በመታገድ በኩል ተገቢውን ሚና ሊጫወት ይገባል ብለዋል ።
11ኛው የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባኤ በዘንድሮ ዓመት በዩኔስኮ ለመመዝገብ ጥያቄ ላቀረቡ 37 የሚደርሱ የማይዳሰሱ ቅርሶች ላይ እንደሚወያይ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።