የገዳ ሥርዓት በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ተመዘገበ

የተባባሩት  መንግሥታት ድርጅት የትምህርት ፣ሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የገዳ ሥርዓትን  በዓለም  የማይዳሰስ  ወካይ ቅርስ አድርጎ  በዛሬው ዕለት መዝግቦታል ።

እየተካሄደ ባለው 11ኛው የዩኔስኮ  የማይዳሰሱ ቅርሶች  ጉባኤ  በዓለም ቅርስነት  ለመመዝገብ  ከቀረቡት  የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል የሆነው አገር በቀል የሆነውና የኦሮሞ ህዝብ የዴሞክራሲ ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት  መገለጫ  የሆነው  የገዳ ሥርዓት ለመመዝገብ  የተቀመጡ መሥፈርቶች በሙሉ በሟሟላቱ በቅርስነት ተመዝግቧል።

በ11ኛው የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባኤ ላይ የተገኙ የበይነ መንግሥታት ኮሚቴ ተወካዮች የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ  ወካይነት  ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት  በሙሉ ድምጽ ድጋፍ የሠጡት  በመሆኑ ሊመዘገብ ችሏል ።

የገዳ ሥርዓት የዓለም ቅርስነት ሆኖ እንዲመዘገብ ለማድረግ ኢትዮጵያ ያቀረበቺው ሰነድ በኮሚቴው ግምገማ መሠረት ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን በተጨማሪነት የገዳ ሥርዓቱን ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችሉ እርምጃዎች  መወሰድ  እንደሚገባቸው  በጉባኤው ውሳኔ ተጠቁሟል ።

የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የገዳ ሥርዓት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላላፍ የሚያስችሉ ሥራዎችን በማከናወን  ረገድ  ቅርሱን በትምህርት ፣ በጥናትና  በተቋማት ጭምር እንዲደገፍ  የማድረጉ ሥራዎች  ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ተመልክቷል ።

ሥርዓቱን በሚገባ ጠብቆ ለማቆየት ህብረተሰቡን ያሳተፈ የባህል ልማት በማካሄድና የህግ ከለላን  ተግባራዊ  በማድረግ  የተሻለ ለባህሉ ዕድገት የተሻለ ሚናን  መወጣት እንደሚቻል  ከጉባኤው  ተሳታፊዎች  ተገልጿል ።

በጉባኤው በተለይም የአንዳንድ አገራት ተወካዮች የገዳ ሥርዓት የማህበራዊ ፣ የዴሞክራሲና  የባህል  መገለጫ  በመሆኑ እንዲሁም  የራሱ ባህላዊ ህጎች ያሉት በመሆኑ ለዓለምን እንደ ተምሳሌትና ማስተማሪያነት  የሚወሰድ  እሴት መሆኑንም  ጭምር  ተናግረዋል ።

ኢትዮጵያ  በዛሬው  ዕለት በዓለም ቅርስነት  ካስመዘገበችው የገዳ ሥርዓት በተጨማሪ የመስቀል ደመራና ከፍቼ  ጨምበላላ  በዓላትን ቀጥሎ  በዩኔስኮ  የማይዳሰሱ ባህላዊ  ወካይ ቅርስነት ማስመዝገቧል ይታወሳል ።