ሙስሊሙ ኀብረተሰብ የተጀመረው ልማት እንዲቀጥል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

ሙስሊሙ ኀብረተሰብ አንድነቱን በማጠናከር የተጀመረው አገራዊ ልማት እንዲቀጥል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።

1 ሺህ 491ኛው የመውሊድ በዓል ትናንት በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ በድምቀት ተከብሯል።   

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ አሚን ጀማል በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከበሩ የታመሙትን በመጠየቅ፣ የታረዙትን በማልበስና የተቸገሩትን በመርዳት ሊሆን ይገባል። 

''ነብዩ መሐመድ እውነት መናገር፣ ይቅር ማለት፣ እንግዳን መቀበልና መፈቃቀር የእስልምና እምነት መሰረታዊ ክፍል መሆኑን ደጋግመው አስተምረዋል'' ብለዋል። 

ሙስሊሙ ኀብረተሰብም የነብዩን አስተምህሮ በመከተል አቅመ ደካሞችን በመርዳትና በመንከባከብ በዓሉን እንዲያሳልፍ አሳስበዋል። 

ምክር ቤቱ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ህዝበ ሙስሊሙ በአገሪቱ የተጀመረው ልማት እንዲቀጥል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

''የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ከበዓልነቱ ባለፈ ለአገሪቱ ዘላቂ ሠላምና ልማት መረጋገጥ ዋነኛ መሳሪያ አድርጎ ሊጠቀምበት ይገባል'' ያሉት ደግሞ  የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሙሐመድ ኑር ሼህ አህመድ ሻፊ ናቸው። 

ለሠላምና ለልማት እንቅፋት የሆነውን አክራሪነትና ጽንፈኝነትን በመታጋል ረገድ የእምነቱ አባቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

በዓሉን እሴቱን በጠበቀ መልኩ ለትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት እንዳላበቸውም እንዲሁ።  

ከበዓሉ ተካፋዮች መካከል ሀጂ ሸምሱ አባስ ''ነብዩ የልማት ተካፋይ ነበሩ፣ የስራ ሰው ነበሩ ሙስሊሙም የእሳቸውን ፈለግ በመከተል ልማቱን ለማፋጠን ቆርጦ መነሳት አለበት'' ብለዋል።  

አባቶች ስለ ሠላም በመስበክና በማስተማር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀው አሸባሪነትን በመዋጋት ረገድ ከወጣቶችም ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።

ሌላኛው የበዓል ተካፋይ ሀጂ ተሻለ ኬሮ የኃይማኖት ጽንፈኝነትና አክራሪነት ምንጩ ድህነት መሆኑን ነው የተናገሩት።

ድህነትን ለማጥፋት ሁሉም መተባበር እንዳለበትና በተለይ ሙስሊሙ ወጣት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።(ኢዜአ)