በኢትዮጵያ በቅርቡ እየተከሰተ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የሚያስከትለው ጉዳት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ገለጸ፡፡
በዩንቨርሲቲው የጂዮ ፊዚክስ የሕዋ ሳይንስና ሥነከዋክብት ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር አታላይ አየለ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ከኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ጋር ተያይዞ መጠኑ የተለያየ ርዕደ መሬት በተለያዩ ሥፍራዎች ቢያጋጥምም የከፋ ጉዳት ባለማስከተሉ ጉዳዩ ትኩረት እንዲነፈገውና ይሄም የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችና ስለአደጋው ያለውን አጠቃላይ ግንዛቤ አነስተኛ እንዲሆን አድርጓል፡፡
አገሪቱ እስካሁን አደጋን የመከላከል ቅኝቷ በአብዛኛው ከድርቅና ከጎርፍ አደጋ ጋር የተያያዘ እንደነበርና አሁን ግን የመሬት መንቀጥቀጥና መንሸራተት ክስተቶች እየተስተዋሉ በመሆናቸው የቅድመ ጥንቃቄ ሥራው ተጠናክሮ በስፋት መሰራት ይገባል ብለዋል፡፡
ከአሥር ወራት በፊት በበሃዋሳ በሬክተር ስኬል 4.3፣ 2002 ዓ.ም. በሆሳዕና፣ በ2003ዓ.ም. በይርጋለም እንዲሁም በ2006ዓ.ም. በወራቤ አካባቢ መከሰቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ክስተቶቹ ያስከተሉት የከፋ ጉዳት ባለመኖሩ ተገቢውን ትኩረት ሳያገኙ መቅረታቸውን ዶክትር አታላይ አስታውሰዋል፡፡ ምንም እንኳን በስምጥ ሸለቆ የሚገኙ የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ከተሞች ካሉበት አካባቢ ተፈጥሮ ጋር ተያይዞ ስጋት ቢኖራቸውም በሌሎች የዓለም ክፍሎች እየደረሰ ካለው አደጋ አንጻር ሲታይ መጠኑ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑም ተገልጿል፡፡
ዶክተር አታላይ እንደገለጹት በምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ፣ ከቀይ ባሕር ስምጥ ሸለቆ እንዲሁም ከኤደን ባሕረ ሰላጤ የሚነሱት ስምጥ ሸለቆዎች መገናኛ የአፋር ዝቅተኛ ሥፍራዎች ከፍተኛ ሙቀት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ሙቀቱን ተከትሎም በመሬቱ ውስጣዊ ክፍል በአለቶች መካከል ከፍተኛ ውጥረት ይፈጠራል ይህም የመሬት መንቀጥቀጥ እንዲከሰት ያደርጋል፡፡
የችግሩ ጉዳት ይነስም ይብዛ ጉዳትን የመቀነስ ቅድመ ጥንቃቄ ማከናወን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ይሄን ደግሞ ከሌሎች የመሰረተልማት ግንባታ ጋር አያይዞ ማስኬድ እንደሚገባም ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ካላት መልከዓምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ስለመሬት መንቀጥቀጥና አደጋ ቢከከሰት ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል? በሚሉ ጉዳዮች ላይ የመገናኛ ብዙሃን ተከታታይነት ያለው ዘገባ ወደ ሕብረተሰቡ ማድረስ እንደሚገባቸው ዶክተር አታላይ አክለው ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ በፊት በደብረ ብርሃን ምዕራባዊ አቅጣጫ ያጋጠመ በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ 6 የተለካው ርዕደ መሬት የከፋ ጉዳት ባያደርስም ንዝረቱ በአንዳንድ የአዲስ አበባ ስፍራዎችን ላይ መሰማቱን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡