ኤጀንሲው በትግራይ ለ7ሺህ ማህበራት የመኖሪያቤት መሬት እንደሚሰጥ አስታወቀ

በትግራይ ክልል 110 ከተሞች በማህበር ለተደራጁ ነዋሪዎች የመኖሪያቤት ግንባታ የሚውል መሬት ለመስጠት እንቅስቃሴ መጀመሩን የክልሉ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ ፡፡

 

የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገረዝግሄር አብረሃ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት በተያዘው ዓመት ከከተማ ልማት ቢሮ በመተባበር በማህበር ተደራጅተው ለመስራት የሚቸሉ ነዋሪዎች መሬት እና የብድር አገልግሎት ለመስጠት ታቅዷል፡፡

 

በክልሉ ከ7ሺህ በላይ ማህበራት ለመስጠት የታቀደ ሲሆን፤ መጀመሪያ ለተወሰኑ ማህበራት ዕድሉን በመስጠት በቀጣይም በከተሞች የነዋሪው ፍላጎቱና የመሬት ይዞታ ታይቶ ስራው እየሰፋ እንደሚሄድ ነው ያመለከቱት  ፡፡

 

በክልሉ በሚገኙት 12 ዋና ዋና ከተሞች ላይ ለእያንዳንዱ በራስአገዝ ህብረት ስራ ማህበር ለሚደራጁ ሰዎች 1ሺ 400  ካሬ ሜትር የሚሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

 

አንድ ማህበር 20 አባላትን ያቀፈ ሆኖ ለእያንዳንዱ ሰው ለሚገነባው ባለአንድ ፎቅ 70 ካሬ ሜትር የሚደርሰው መሆኑን አብራርተዋል ፡፡

መኖሪያቤቱም  ከታች ሳሎን፣ ሽንትቤትና ኩሽና ያለው ሲሆን ከላይ ደግሞ ባለሶስት መኝታቤቶች ይኖሩታል ነው ያሉት  ፡፡

 

በክልሉ ታዳጊ አንድ 25 ከተሞች  ላይ ለአንድ ሰው 140 ካሬ ሜትር የሚያገኝ ሲሆን፤ በታዳጊ ሁለትና ታዳጊ ሶስት ተብለው በተፈረጁት 73 ከተሞች ለሚኖር ደግሞ 200 ካሬ ሜትር መሬት እንደሚሰጠው ገልጸዋል  ፡፡

 

በነዚህ ታዳጊ ከተሞች በመደዳ ወደ ጎን እንደየ ዓቅማቸው ቤት መገንባት እንደሚችሉ ነው ያስረዱት ፡፡

 

መሬቱ የሚሰጠውም የከተማው ነዋሪ የሆነ ፣በትዳር አጋሩም ቢሆን የራሱ ቤት የሌለውና ቋሚ ገቢ ያለው  መሆን እንዳለበት ነው ያስታወቁት ፡፡

 

ቤቱን ለመገንባት ዓቅም ያለው 50 በመቶ ገንዘብ በባንክ ዝግ አካውንት ማስቀመጥ እንዳለበትም በመጠቆም ፡፡

 

መኖሪያቤቱን ለመገንባት ዓቅም የሌለው ሰው ደግሞ 20 በመቶ በመቆጠብ 80 በመቶ ደግሞ ከደደቢት ወይም  ከአደዳይ የብድርና ቁጠባ አክስዮን ማህበራት ሊያገኝ እንደሚችል ገልጸዋል  ፡፡

 

በመንግስት የሚሰጠው መሬት ልዩ የሚያደርገው የአከባቢው ህብረተሰብ መሬት መርገጥ አለብኝ የሚለው ጥያቄና ፍላጎት የሚደግፍ  በመሆኑ ነው ብለዋል ፡፡

በሀገር እና በክልል ደረጃ ተይዞ የነበረው የኮንዶሚንየም ግንባታ ዕቅድ ግን ሰፊ የፋይናስ አቅርቦት እና በቂ ዝግጅት የሚያስፈልገው ስለሆነ ዘንድሮ ለቀጣይ ከመዘጋጀት ውጪ ምንም ዓይነት ስራ እንደማይኖር አቶ ገረዝግሄር አስታውቀዋል ፡፡