የትራፊክ አደጋ ከበሽታዎች ባልተናነሰ ሁኔታ በዓመት ከ4ሺህ እስከ 5ሺህ ሰዎችን እየጨረሰ መሆኑን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አሳሰቡ ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትራፊክ አደጋ ለመቀየር የህዝብ ንቅናቄ ለማድረግ መታቀዱን ይፋ አድርገዋል ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ዛሬ በተካሄደው 12ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ የትራፊክ አደጋው በወረርሽኝ ምክንያትም ሆነ በተለያዩ በሽታዎች እንኳ አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ሰውን አይጨርሱም ነው ያሉት ፡፡
በተለይም ሆስፒታሎች በአደጋው በሚገቡ በርካታ ሰዎች በጣም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብተዋል ብለዋል ፡፡
በከተማና በገጠር የሰው ህይወት እየጠፋ ያለው በመኪና ብቻ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ጋሪዎችና ብስክሌቶች ብዙ ሰው እየገደሉ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡
ስለዚህ የተሽከርካሪዎች ሁኔታና የዘመናዊ የትራፊክ ማኔጅመንት ላይ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል ፡፡
ከዕድገታችን ጋራ የሚታዩ ጉዳዮች መኖራቸውን ያመለከቱት አቶ ሃይለማሪያም ፤ በሀገራችን ከ100 ዓመት በፊት አንስቶ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 150ሺህ ተሽከርካሪዎች የነበሩት ዓምና ብቻ 110ሺህ ተሽከርካሪዎች መግባታቸውን አመልክተዋል፡፡
ዘንድሮ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ባልተለመደ መልኩ በምሳ ሰዓት ጭምር የትራፊክ መጨናነቅ እየገጠመ በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ፈተና ሆኗል ነው ያሉት ፡፡
ስለሆነም ከአዳዲስ ዕድገት ጋራ የሚመጥን የትራፊክ ማነጅመንት፣ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ከአሽከርካሪዎች ብቃት ጋር የተያያዘ ስራ መስራት ይጠይቃል ነው ያሉት ፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የአሽከርካሪዎች ብቃት የሚወስነው ደግሞ ሌሎች ያደጉ አገሮች እንደሚያደርጉት ከትምህርት ካሪክለም ጀምሮ ነው ማስተማር የሚያስፈልገው ፡፡
በሀገሪቱ በህገ ወጥ መንገድ የመንጃ ፍቃድ የሚሰጥበት ሁኔታ መቀየር አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ይህ ካልሆነ አደጋው ተባብሶ ይቀጥላል ሲሉ ነው ያስገነዘቡት ፡፡
በተለይም በህብረተሰቡ ውስጥ መንጃ ፍቃድን በአቋራጭ ያመጣ ሰው መወገዝ ሲገባው እንደ ጀግና እየታየ ይከበራል ብሏል፡፡
ስለሆነም ከኤች አይ ቪ ኤድስ ያልተናነሰ ህዝባዊ ንቅናቄ በማካሄድ ሁኔታውን ለመቀየር በዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኘው የመንግስት አመራር እና የምክርቤት አባላት ከህገ-መንግስታዊ ስራቸው ጋር በማቀድ በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ በህዝባዊ ንቅናቄው ላይ እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡